ቀጥታ፡

ምክክሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል እሳቤና ዝግጁነት የተሰነቀበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው- ምሁራን

ቦንጋ፣ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የጋራ እሳቤ የተሰነቀበትና ለሀገር ግንባታ የዜጎች ሁሉ ዝግጁነት የታየበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን የታሪክና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።

በአዲስ አበባ የተካሄደውና ከመላ ሀገሪቷ የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ጉባኤተኞች የተሳተፉበት የምክክር ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል።

የዘንድሮውን አዲስ ዓመት የተቀበልነው ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የጋራ ቃል ኪዳን የተሰነቀበት ታሪካዊ ጉባኤ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው። 

በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ በመሰነቅ፤ በህብረ ብሄራዊ አብሮነት በመድመቅ የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በመቀበል ሌላ የህይወት ምእራፍ የተጀመረበትም ነው ማለት ይቻላል።

የዘንድሮው አዲስ ዓመት ኢትዮጵያዊያን በችግሮቻቸው ላይ መክረው ለመፍትሄው የጋራ አቋም የያዙበት፤ አዲስ መንግስት የሚመሰረትበትና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ሂደት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው። 

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን፤ አዲሱ ዓመት በምክክር የተሸጋገርንበትና እንደ ዜጋም ለሀገራዊ ልማት ትልቅ ተስፋ የተሰነቀበት ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካና አለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል መምህር ዘሪሁን ያሬድ፤ ለሀገራዊ ችግሮች እልባት ለማበጀት ምክክርን ሁነኛ መፍትሄ ለማድረግ ወደ ምክክር መገባቱ በራሱ ዘመናዊ እሳቤ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም ስኬታማ መሆን የተቻለበት ታሪካዊ አጋጣሚ መፈጠሩን አንስተው በችግሮች ላይ መክረንና ለእልባቱ ተዘጋጅተን ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገራቸው ለሁላችንም ትልቅ ተስፋ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የጋራ እሳቤ የተሰነቀበትና ለሀገር ግንባታ የዜጎች ሁሉ ዝግጁነት የታየበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

የምክክሩ ዓላማ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታት ጥረት መሆኑን አንስተው ከሃይል አማራጭ ይልቅ በውይይት የሚያምን ትውልድ በመፍጠርና ሀገር በመገንባት ሂደትም ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ሰለሞን ማሞ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የግጭትና የጦርነት አዙሪት የሚያበቃበትን እድል የፈጠረና ምክክር የችግሮች ሁሉ አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ሁሉም የተረዳበት መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክሩ የታየውና ሁላችንም የተገነዘብነው የዜጎች እሳቤ ከምንም በላይ ሀገርን ያስቀደመና ለችግሮች ሁሉ ዘላቂ መፍትሄን መሻት መሆኑን ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአዲስ ዓመት፤ አዲስ ተስፋ በመሰነቅ ለተመከረባቸው አጀንዳዎች በሂደት ተፈፃሚነት በጋራ መትጋት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም