ቀጥታ፡

በትምህርት ቤቶች እና በወላጆቻችን በተደረገልን ድጋፍና ክትትል ስኬታማ ሆነናል -ተማሪዎች

ወልድያ፣ መስከረም 7/2019  (ኢዜአ):- በትምህርት ቤቶች እና በወላጆቻችን የተደረገልን ድጋፍ ስኬታማ በመሆን ትምህርታችንን ለመቀጠል አስችሎናል ሲሉ የሰሜን ወሎ ዞን ተማሪዎች ገለጹ።

በሰሜን ወሎ ዞን በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች የእውቅናና ሽልማት መርሃ-ግብር አካሂዷል።

በሰሜን ወሎ ዞን የ12ኛ ክፍልና የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በትምህርት ቤቶችና በወላጆች የተደረገልን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ጥሩ ውጤት አምጥተን ለቀጣይ ትምህርት እርከን እንድንዘጋጅ አግዞናል።

ከዚህ ውስጥም በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 567 ነጥብ 44 ያመጣው የቆቦ ከተማ «ዕውቀት ጮራ» ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ መንገሻ ሞላ፤ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተመቻቸው የአዳሪ ትምህርት ቤት እድል ተጠቃሚ መሆኑን ነው የሚናገረው።

በዚሁ ወቅት በተለይ በመምህራን በተደረገለት ድጋፍ ጠንክሮ በመስራት ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃውን ውጤት ለማስመዝገብ እንዳስቻለው ነው የሚናገረው።

በቀጣይም የሕግ ትምህርት በመከታተል ያስተማረውን ማህበረሰብ የማገልገል ህልም እንዳለው ነው የገለፀው።


 

በተመሳሳይ በዚሁ ትምህርት ቤት በ12ኛ ክፍል ፈተና 544 ነጥብ 67 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያመጣው ተማሪ ኃየሎም አስረስ፤ በወላጆች፣ በትምህርት ማህበረሰቡና በመንግስት በተደረገለት ድጋፍ ጥሩ ውጤት ላመጣ ችያለሁ ነው የሚለው።

በሌላ በኩል ተማሪ ብሩህ ሄኖክ በ6ኛ ክፍል የዞን ፈተና 97 ነጥብ 5 ያስመዘገበ ሲሆን ለዚህም የመምህራን እንዲሁም  የቤተሰብ ድጋፍ ለውጤቱ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልፅዋል፡፡


 

የሰሜን ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አክሊሉ እንደገለጹት፤ በዞኑ በ2018 ትምህርት ዘመን 825 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት አምጥተዋል።


 

ውጤቱ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር የ7 በመቶ እድገት እንዳለው ነው የገለጹት።

ለውጤቱ መመዝገብም የትምህርት ቤቶች ልዩ ድጋፍ፣ የቤተ-መጽሐፍትና የኮምፒውተር ግብአቶች መሟላት አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው የጠቀሱት።

በአዲሱ የ2019 የትምህርት ዘመንም የኦንላይን ፈተና ዝግጅቶችን ጨምሮ የማጠናከሪያ ሥራዎችም በተሻለ መልኩ እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም