የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2019 (ኢዜአ):- ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሩዋንዳ ጋር ዛሬ ታደርጋለች።
ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም በታንዛንያ አስተናጋጅነት መካሄድ ጀምሯል።
በውድድሩ ላይ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ታንዛንያ እና ሩዋንዳ ጋር ተደልድሏል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል።
በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በሐምሌ ወር 2018 ዓ.ም ከተጀመረው ብሔራዊ ምልመላና ምዘና( National Camping) አንስቶ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለታንዛንያው የሴካፋ ማጣሪያ ውድድር መጀመሪያ ላይ የ40 ተጫዋቾችን ጊዜያዊ ስም ዝርዝር ይፋ አድርጎ ነበር።
በአሁኑ ወቅት አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ስብስቡን ወደ 25 ተጫዋቾች በመቀነስ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቶ ወደ ስፍራው አቅንቷል።
በአንድሬ ካሳ ምቡንጎ የሚመራው የሩዋንዳ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ በአዘጋጇ ታንዛንያ 3 ለ 0 ተሸንፏል።
የሩዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበጀት እጥረት ምክንያት ቡድኑ በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፍ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ ከሀገሪቷ ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በተደረገ ስምምነት ውሳኔው ተቀይሮ ውድድሩ ሊጀመር የአንድ ሳምንት እድሜ ሲቀረው መሳተፉ ተረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ጉዞውን በድል ለመጀመር ይጫወታል።
በአንጻሩ የሩዋንዳ አቻው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ያለውን ተስፋ ለማለምለም እጅጉን ወሳኝ ነው።
በቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ታዳጊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን መስከረም 9 ቀን 2019 ዓ.ም ከአዘጋጇ ታንዛንያ ጋር ያደርጋል።
ቡድኑ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚገባው ከምድቡ አንደኛ ወይም ከሶስቱ አጠቃላይ ምድቦች ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ ብቻ ነው።
በምድብ ሁለት ዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ እንዲሁም በምድብ ሶስት ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ብሩንዲ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በጋና እ.አ.አ በ2027 ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣሪያ ውድድሩ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ይኖርበታል።
ከየቀጣናው ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ያልፋሉ።
ብሔራዊ ቡድኑ በጋና በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑ ካለፈ እና ግማሽ ፍጻሜ መድረስ ከቻለ በዛው ዓመት በአዘርባጃን እና ኡዝቤኪስታን ጣምራ አዘጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማለፉን ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በ20 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጊዜ ተሳትፋለች።
እ.አ.አ በ1993 በሞሪሺየስ በተካሄደው እንዲሁም እ.አ.አ በ2001 ራሷ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፋለች።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።