ቀጥታ፡

የተማሪዎች ምገባ አያሌ ትሩፋቶች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ466 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህጻናት በትምህርት ቤት የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች የምግብ አማራጭ ብቻ ሳይሆኑ በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ላይ ያላቸው አዎንታዊ ተጽእኖ እጅግ የገዘፈ ነው።

መርሃ ግብሩ የተማሪዎችን የመማር ምጣኔ በመጨመር በተቃራኒው መጠነ ማቋረጥን በእጅጉ በመቀነስ ረገድ ጉልህ ፋይዳ አለው።

ፕሮግራም በተለይም በአደጋ ተጋላጭና ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡ ልጆችን ቁጥር እንዲጨምር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ተማሪዎች በቀን ውስጥ የሚያገኙት የተመጣጠነ ምግብ በክፍል ውስጥ ያላቸውን የንቃት፣ የማስታወስ እና የትምህርት መቀበል አቅም በማሳደግ የትምህርት ውጤታቸውን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል።

የኢትዮጵያ የህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) እና የዓለም የምግብ ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ምገባው ህጻናት ከስድስቱ የምግብ ምድቦች የተውጣጡ አልሚ ምግቦችን እንዲያገኙ በማድረግ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትንና የጤና አደጋን ይቀንሳል።

የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦቱ የህጻናትን አጠቃላይ አካላዊ እድገት፣ የበሽታ መከላከል አቅም (Immunity) እና የአዕምሮ ጤና በመጠበቅ ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር የሚያስችል ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እ.አ.አ በ2030 ሁሉም ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ አቅዶ እየሰራ ይገኛል።


 

በአፍሪካ ደረጃ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህጻናት የተለያዩ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሮች ተጠቃሚ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያም የትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ ግብር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ከ9 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑን ገልጸው፤ ሀገሪቱ የምትመግበው ህጻናት ቁጥር ከአንዳንድ ሀገራት የህዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዳጊ ህፃናት ትምህርት ቤት መሄድ ሲገባቸው በዳቦ ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ ሊተኮርበት የሚገባ ዋነኛ የሀገር ግንባታ ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ የምገባ ኤጀንሲ በማቋቋም ተማሪዎችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የማድረግ ዘላቂ ተግባር በስኬት በመከናወን ላይ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በመዲናዋ በሚገኙ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከቅድመ-አንደኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ለሚማሩ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ (ቁርስ እና ምሳ) በነፃ ይመገባሉ።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሞክሮ በመነሳት ይህ ስራ በፈረንሳይ ፓሪስ እና በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ በተከናወኑ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተወዳድረው አሸናፊ በመሆን የሜላን ፓክት ሽልማት (Milan Pact Award) ተቀዳጅቷል።

እ.አ.አ በ2022 በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ በተካሄደው 8ኛው የዓለም አቀፍ የከተሞች የምግብ ፖሊሲ ስምምነት ጉባኤ ላይ የተበረከተው ይህ ታሪካዊ የሜላን ፓክት ሽልማት፣ አዲስ አበባ መርሃ ግብሩን በዘላቂነትና በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ዘርፍ እጅግ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመምራቷ የተሰጠ ነው።

በተጨማሪም እ.አ.አ በ2021 በጣሊያን ሮም በተካሄደው የዓለም ሥነ ምግብ ኮንፈረንስ እና በሚላን የምገባ ፎረም ላይ መዲናዋ የምገባ ፎርም ምርጥ ተሞክሮ በሚል እውቅና አግኝታለች።

እነዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች የተሰጡት መርሃ ግብሩ የተማሪዎችን የምገባ ችግር ከመቅረፍ ባለፈ፣ ከተማዋ የምግብ ስርዓትን በዘላቂነት በመምራትና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን እናቶች በህብረት ስራ ማህበራት በማደራጀት ማህበራዊ ፍትህና የኢኮኖሚ ነፃነት እውን እንዲሆን በማድረጓ ነው።

የአዲስ አበባ አርአያነት ያለው ተግባር አሁን ላይ ወደ ክልሎች እና ከተሞች በስፋት እየተዳረሰ ይገኛል፤ እንደ ኬንያ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የልዑካን ቡድኖችም መዲናዋን በመጎብኘት ልምድ እየቀሰሙ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን የተመለከተ አዲስ የስነ ምግብ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ተግባራዊ አድርጓል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ መርሃ ግብሩ ተማሪዎች በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ይሰማቸው የነበረውን የስነ-ልቦና ጫናና የድፍረት ማጣት ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ ማህበራዊ ፍትህ ማረጋገጡን በአንድ ወቅት ገልጸዋል።

ምግብ በማብሰልና በማቅረብ ሂደት ላይ ከ25 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶች በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ በማድረግ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ገንብቷል።

የትምህርት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በሀገር አቀፍ የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብሩ አብዛኛው በጀት በሀገር ውስጥ አቅም እና በመንግስት የሚሸፈን ነው።

መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ በተለይም ድርቅና የአየር ንብረት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተማሪዎች ምዝገባ በ10 በመቶ እንዲጨምር እና የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔ በእጅጉ እንዲቀንስ አድርጓል።

ትምህርት ቤቶች የወጪ ጫናቸውን እንዲቀንሱ በትምህርት ቤቶች ግቢ ውስጥ የጓሮ አትክልት ልማት፣ የዶሮ እና የወተት ከብቶች እርባታ እንዲጀመር ተደርጓል።

ኢትዮጵያ ይሄን መርሃ ግብር የምግብ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሀገርን የረጅም ጊዜ የሰው ሀብት (Human Capital) መገንቢያ ስትራቴጂ አድርጋ እየሰራች ይገኛል።

የምገባ ፕሮግራሙ ከትምህርት ተደራሽነትና ውጤታማነት ባሻገር ህጻናት በጤናማ አካልና አእምሮ እንዲያድጉ በማድረግ ለሀገር አቀፍ የጤና ጥበቃ ስራዎች ትልቅ አበርክቶ እያበረከተ ይገኛል።

በምገባ ማዕከላት ዙሪያ የሚደረጉ የንፅህና አጠባበቅና የደህንነት ትምህርቶች ተማሪዎች በለጋ እድሜያቸው ጤናማ የኑሮ ዘይቤዎችን እንዲላመዱና የግል ንፅህናቸውን እንዲጠብቁ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።

በአጠቃላይ የምገባ ፕሮግራም በትምህርት ላይ እያሳረፈ ካለው በጎ አሻራ ባለፈ ምርታማ ትውልድ ለመፍጠር እና ለአንድ ሀገር እድገት እና ልማት ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ በስኬት ጎዳና እና ለሌሎች አርአያ በሚሆን ተምሳሌታዊ ተግባር በግንባር ቀደምትነት የምትነሳ ሀገር ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም