ቀጥታ፡

ግብፅ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የዓባይ ተፋሰስ እውነታ መቀበል አለባት - አምባሳደር ተሾመ ቶጋ

ዓባይ ወንዝ የተፋሰሱ ሀገራት የሚጋሩትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም ከሆኑ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶች ውስጥ የሚመደብ ነው።

ግብፅ በወንዙ ፍሰት ላይ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ ሳታበረክት የታችኛው ተፋሰስ ዋና ተጠቃሚ ሆና ቆይታለች። ኢትዮጵያ ደግሞ፣ የዓባይ ወንዝ የውሃ ፍሰት 86 በመቶ ድርሻ አላት።

በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ተሾመ ቶጋ በ«ፐልስ ኦፍ አፍሪካ» (Pulse of Africa) መድረክ ላይ “Egypt Must Align Its Nile Strategies with the Realities of 21st Century” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ግብፅ በወንዙ አጠቃቀም ላይ “ታሪካዊ መብቶች አሉኝ” በሚል አቋም ለረጅም ጊዜ መያዟን አመልክተዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፣ ግብፅ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ይሁንታ በሌለበት የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ላይ የሙጥኝ ማለቷ ከዘመኑ ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ መርሆዎች ጋር የሚስማማ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ትልቅ ዕንቅፋት ሆኗል።

እ.አ.አ በ1959 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ውል የዓባይን አጠቃላይ የውሃ ድርሻ የሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን ባላሳተፈ መልኩ ለግብፅና ሱዳን ብቻ የሰጠ መሆኑን አምባሳደሩ አውስተዋል።

መሰረታዊ መነሳት ያለበት ጥያቄ «ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት ፍላጎት ሳይሆን፣ ያ ፍላጎት የሌሎችን የተፋሰስ ሀገራት ፍትሐዊ መብቶችና የልማት ትልሞችን በሚጎዳ መልኩ መፈጸም አለበት ወይ?» የሚለው ነው ብለዋል።

የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የምግብ ዋስትና ስጋቶች እና አዳዲስ የኢነርጂ ፍላጎቶች የዓባይ ወንዝ አስተዳደርን መሰረታዊ በሚባል ሁኔታ መቀየራቸውን አንስተዋል።

የዓባይን ወንዝ በቀድሞ ታሪካዊ ውሎች ብቻ መመልከት ከእውነታው የራቀ እና ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የማይችል አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ በጽሑፋቸው እንዳመላከቱት፣ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ የውስጥ አቅሟን አስተባብራ የልማት ግቦቿን ማሳካት እንደምትችል ያረጋገጠ ትልቅ ምዕራፍ ነው።

ይህ ፕሮጀክት በወንዙ ላይ የነበረውን የኃይል ሚዛን እና ስትራቴጂካዊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መለወጡንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ተጨማሪ ልማት ማካሄድ የለባትም የሚሉ ሀሳቦች ተቀባይነት እንደሌላቸው ጠቅሰው፤ የፋይናንስ ክልከላዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን የልማት ፕሮጀክቶች ማስተጓጎል ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን የሕዳሴው ግድብ በተግባር ማሳየቱን ገልጸዋል።

አሁን ያለው ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ የሁሉንም ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት የሚያስተናግድ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ማዕቀፍ መፍጠር መሆኑን አስገንዝበዋል።

እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ከጎረቤቶቻቸው ጋር በውይይትና በድርድር እንደሚያለሙት ሁሉ፣ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራትም ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ማስተዳደር እንደሚችሉ የሌሎች ወንዞች ተሞክሮዎችን በመጥቀስ አምባሳደሩ አብራርተዋል።

የተፋሰሱ ሀገራት እ.አ.አ በ2010 ይፋ ባደረጉት እና እ.አ.አ በ2024 በሕጋዊ መንገድ ጸድቆ ሥራ ላይ በዋለው አካታች የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) አማካኝነት እያደረጉት ያለው ጥረት የላይኛው የተፋሰሱን ሀገራት ፍላጎትና ልማት መከበር እንዳለበት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ ከግድቡ ወይም ከኢትዮጵያና ግብፅ የሁለትዮሽ ግንኙነት የዘለለና የዘመኑን የኢኮኖሚና የውሃ አስተዳደር እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

የእ.አ.አ 1993ቱ የጋራ መግባቢያ ስምምነት እና የእ.አ.አ 2015ቱ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት (Declaration of Principles) ኢትዮጵያ ሰላማዊ መፍትሔዎችን ለመፈለግ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን እና ግብፃውያን ጥልቅ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር እንዳላቸው አምባሳደሩ ገልጸው፤ ዓባይን እንደ ጠብ መጫሪያ ሳይሆን የሕዝቦች ማስተሳሰሪያ ድልድይ በማድረግ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ እንዳብራሩት፣ የኢትዮጵያ የሰላም እና የትብብር መንፈስ እንደ ድክመት ወይም መብትን አሳልፎ እንደ መስጠት ሊወሰድ አይገባም።

ኢትዮጵያ ድህነትን የማስወገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ እና ለኢኮኖሚ የመጠቀም ሕጋዊ መብት አላት። ከዚህ ጎን ለጎንም በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የውሃ ሀብቷን በፍትሐዊነት ለመጠቀም ትሰራለች ነው ያሉት።

የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ጉዳይ በአሸናፊነትና በተሸናፊነት ላይ የተመሰረተ የውድድር መልክ መያዝ እንደሌለበትና ትክክለኛው አካሄድ በጋራ ትብብር መንፈስ መስራት መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያና ግብፅ በሃይድሮሎጂ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ፣ በድርቅና አውሎ ነፋስ አደጋዎች መከላከል፣ በግብርና ምርታማነት እና በኤሌክትሪክ ኃይል ንግድ በጋራ መስራት የሚችሉባቸው እድሎች እንዳሉ አምባሳደሩ አንስተዋል።

ሀገራቱ በሃይድሮፓወር እና በውሃ ሀብት አስተዳደር በትብብር መስራት እንደሚችሉም አመልክተዋል።

የኢነርጂ ንግድ፣ የኢንቨስትመንት ትስስር እና የቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሁለቱ ሀገራት ወንዙን እንደ የጋራ የልማት ዕድል እንዲጠቀሙበት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ግብፅ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የዓባይ ተፋሰስ እውነታ መቀበል እንዳለባትም ነው የተናገሩት።

አሁን የሚያስፈልገው ግጭት ሳይሆን፣ በሉዓላዊ መብት፣ በፍትሐዊ አጠቃቀም፣ በጋራ መከባበር እና በጋራ ብልጽግና መርሆዎች ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ መግባባት መፍጠር ነው ብለዋል አምባሳደሩ።

ዓባይ የአንድ አካል ብቸኛ ባለቤትነት የሚንጸባረቅበት ሊሆን አይገባም ያሉት አምባሳደሩ፤ የወደፊት የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚገነባው በጋራ ኃላፊነት እና ትብብር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም