በዞኑ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ገንዳውኃ፣ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ የዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
ዞኑ "አርቆ ማየት፣ አልቆ መስራት" በሚል መሪ ሀሳብ ለሶስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን የ2018 የበጀት ዓመት የስራ እቅድ ግምገማ እና የ2019 የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ አጠናቋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በወቅቱ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተከናወኑ የዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በቅንጅት ይሰራል።
በያዝነው በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማፋጠን የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በበለጠ ትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የማስፋፋት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ማሩ በበኩላቸው፤ በፓርቲው አመራር ሰጪነት የዞኑን ሰላምና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ይበልጥ በትጋት ይሰራል ብለዋል።
ዞኑ ለግብርና ልማት ያለውን ከፍተኛ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን ማስፋፋት ላይ በትኩረት ይሰራል ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ ናቸው።
ለዚህም የግብርና ቴክኖሎጂ፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ ማሰራጨት ላይ ቅንጅታዊ ተግባራት እንደሚጠናከሩ አመልክተዋል።
በተጨማሪም የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለማስተዋወቅና ለማዳረስ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በመድረኩ በተጠናቀቀው በጀት አመት የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች የእውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።