ቀጥታ፡

የቱሪዝም ትንሳኤን ያበሰረው የመደመር እሳቤ

ኢትዮጵያ አስደማሚ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት ናት ።  

የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ደጋግመው ቢያዩዋቸው ፣ ቢታደሙባቸው የማይሰለቹ ተጠንተውም የማያልቁ ፀጋዎች ቢኖሯትም ለዘመናት በወጉ ሳትገልጣቸው የሚጠበቀውን ያክልም ሳይጎበኙ ሳይተዋወቁም ቆይተዋል።

ይህን ባለማድረጓ ደግሞ ከዕልፍ የቱሪዝም ጸዋጋዎቿ ሳትቋደስ ዘመናትን ተሻግራለች።

“በታሪክም ሆነ በተፈጥሮ ጸጋዎች ከኛ ጋር ሊወዳደሩ የማይችሉ ብዙ ሀገራት ከኢንዱስትሪው ብዙ አትርፈዋል። እኛ ግን እንቁዎቻችንን ደብቀን ታሪካችንን አቧራ አልብሰን ለዘመናት ቆይተናል።” የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 259

ዛሬ ግን ይህ ታሪክ እየተቀየረ ነው። ከመደመር መንግሥት አምስት ወሳኝ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በሆነው ቱሪዝም  ቅርሶችንና ወሳኝ ፀጋዎችን ከቁስ ወደ ቁርስ እየለወጠ፣ ኢትዮጵያን እየገለጠ እንዲመጣ እየተደረገ ነው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአራት ኪሎ ቤተመንግስት “ሀ” ተብሎ የተጀመረው አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት በገበታ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ወደ ሁሉም የሃገራችን ክፍሎች ተዳርሷል።

በኢትዮጵያ ትኩረት ተነፍጓቸው የነበሩት የሀገራችን የቱሪዝም ሀብቶች በመደመር መንግሥት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ትንሳኤያቸው ተበስሯል።

ለዘመናት አቧራ ለብሰው የኖሩ ዕንቁ የቱሪዝም ሀብቶች አቧሯቸው እየተራገፈ ነው።

ከዳሎል እስከ ስሜን ተራሮች ማራኪ ተፈጥሯዊ መስህቦች ይበልጥ ለዓለም እየተዋወቁ ነው።

አዳዲስ ተፈጥሯዊ ፀጋዎችም በቱሪዝም ልማት ኢኒሼቲቮች የመገለጥና የመታወቅ ዕድል አግኝተዋል።

የመደመር እሳቤ የምናብ ከፍታና የመፈጸም ልክ አንዱ ጉልህ ማሳያ የቱሪዝሙ ዘርፍ ፕሮጀክቶች ናቸው።

ከነዚህ ኢኒሼቲቮችም መካከል አንዱ ከቤተ መንግስት እደሳት ጀምሮ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ያደረጋት የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ነው።

የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የቱሪዝም አብዮትን በመቀስቀስ የአንድነት ፓርክን፣ እንጦጦና ወዳጅነት ፓርክና ሌሎች ተያያዥ ፕሮጀክቶችን ዕውን አድርጓል።

ዛሬ ላይ አዲስ አበባን አዲስ መልክ አጎናጽፎ፤ የነተቡ ሰፈሮች ወደ ውብ መልኮች ተቀይረው የሚሊዮኖች ጎብኚዎች መዳረሻ ሆነዋል።

ከገበታ ለሸገር በመቀጠል የኢትዮጵያን አዳዲስ መልኮች የገለጠው ኢኒሸቲቭ ደግሞ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ነው።

ገበታ ለሀገር ከኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ወንጪን፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዳውሮና ኮንታን የሸፈነው ኮይሻን፣ከአማራ ክልል የጣናን ምዕራባዊ ዳርቻ የተንተራሰችውን ጎርጎራን ውብ አድርጓል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን አይነተ ብዙ ታሪክ፣ ተፈጥሮንና ባህል በመግለጥ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ሞገስና ድምቀት ሆነዋል።

ከገበታ ለሀገር ቀጥሎ ገቢራዊ የተደረገው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አድማሱ በሶማሌ ክልል ሸበሌ ሪዞርትን፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የደንቢ ኢኮ ሎጅን፣ በአማራ ክልል የሐይቅ ሎጎ ሪዞርትን፣ በአፋር ክልል የኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ እንዲሁም የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርትን እውን አድርጓል።

ከገበታ ለሸገር እስከ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ባሻገር የመደመር መንግስት ታሪካዊ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ እሴት ጨምሮ የመግለጥ አኩሪ ስራዎችንም አከናውኗል።

ለዚህ ደግሞ ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ጀምሮ ጥንታዊ አብያተ መንግስታት፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ተጠግነዋል።

የባለፉት ጥቂት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፍ ለውጦች የኢትዮጵያን ገጽታ ያስተዋወቁ፤ በየአካባቢው ተስፋና ልማትን የፈነጠቁ፣ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች ናቸው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ የዕድገትና የብልጽግና ታሪክ ውስጥ በደማቁ የሚጻፉ አንቀጾች ሆነው ለትውልድ የተኖሩ ዓሻራዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም