የኢትዮጵያና እስራኤል ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ ተሸጋግሯል-አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና እስራኤል ትብብር ወደ ላቀ ምዕራፍ ተሸጋግሯል-አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና እስራኤል ሁሉን አቀፍ ትብብር መጠናከር የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ማሸጋገሩን በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ።
አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጥልቅ ታሪካዊ መሠረት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ግንኙነቱ አሁን ላይ በመንግሥታት ትብብር፣በኢንቨስትመንት፣በቴክኖሎጂ እና በሰዎች አቅም ግንባታ ላይ የተመሠረተ ሁሉን አቀፍና ዘመናዊ አጋርነት ላይ መድረሱን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ እና እስራኤል ከጥንት ጀምሮ የነበራቸው ልዩ ታሪካዊ ግንኙነት ዛሬ ለደረሰበት ጠንካራ የሁለትዮሽ አጋርነት እንዳበቃቸው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ የሁለቱን አገራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማጠናከርና ለማስፋት በተለያዩ ዘርፎች በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።
የሁለቱ አገራት አበይት የትብብር መስኮች አንዱ የሆነው ግብርና፤ የእስራኤል ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኩባንያዎችን በመገንባት ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ባለሙያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያስገቡ መልካም አጋጣሚን መፍጠሩን ነው ያነሱት።
የእስራኤል ኩባንያዎች በፍራፍሬና በአትክልት ልማት ላይ የተሰማሩባቸውን በቢሾፍቱ አካባቢ የሚገኙ የግብርና ስራዎች በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በዘርፉ ያለው ትብብርና ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ አቮካዶን ጨምሮ የግብርና ምርቶቿን ወደ አውሮፓ እና እስያ ገበያዎች የምታቀርብበትን አቅም እንዲያድግ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል አምባሳደር አብርሃም።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጭ ባለሀብቶች፣ እስራኤላውያንን ጨምሮ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።
የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ረገድ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት አምባሳደሩ፤ የተደረጉት ማሻሻያዎች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመመልከት እያገዟቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የማዕድን አቅምን ጨምሮ የኢትዮጵያ ተፈጥሮ ሀብቶች ተጨማሪ የእስራኤል ኢንቨስትመንቶችን መሳብ የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
የእስራኤል ኩባንያዎች ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ ማዕድናት ፍለጋና ማምረት ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ጤና ሁለቱ አገራት ትብብራቸውን እያሰፉባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ የእስራኤል ሀኪሞች ከኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት የአቅም ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መስኮች፣በተለይም በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ያለውን ትብብር አምባሳደሩ አንስተዋል።
እስራኤል የሳይበር ደህንነት ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ረገድ ያከማቸችውን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል እንደምትሻም ተናግረዋል።