በአፋር ክልል የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር የሚደረግ የቅንጅት ስራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር የሚደረግ የቅንጅት ስራ ይጠናከራል
ሰመራ፣መስከረም 6/2019 (ኢዜአ) ፡- በአፋር ክልል የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር የሚደረገው የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በአይሳኢታ ከተማ አስተዳደር ኘላን ኢንተርናሸናል በተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ወጪ የተገነባን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አስመርቆ ወደ ስራ አስገብቷል።
በምረቃ ሰነ ሰርዓቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሳ አደም እንደተናገሩት የአርብቶ አደሩን የትምህርት ተደራሸነትና ጥራት ለማረጋገጥ ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራ ነው።
በዚህም በክልሉ 35 ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ሕጻናት ለመደበኛው ትምህርት የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩና ተነሳሽነታቸው እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽነት የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ዛሬ የተመረቀው ትምህርት ቤትም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል ።
የአይሳኢታ ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ አሚን ያሲን በበኩላቸው የትምህርት ቤቱ ግንባታ የህፃናትን በቅርበት የመማር እድል ያሰፋል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በኘላን ኢንተርናሽናል የአፋር ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት ድርጅቱ ለትምህርት ዘርፉ መሻሻል በግብአት አቅርቦትና በሌሎች አገዛ እያደረገ ነው ብለዋል።
በአይሳኢታ ከተማ አስተዳደር ለሚገኘው ሲንብሌ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል።
በምረቃ ሰነ ሰርዓቱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኀላፊዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።