ቀጥታ፡

ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል

ደሴ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፡-የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻልና አሰራርን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የዞኑ ጤና መምሪያ በደሴ ከተማ ለህብረተሰቡ የተሻለ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መድረክ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር  እያካሄደ ይገኛል።


 

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን በመድረኩ እንደገለጹት፤ የጤና ተደራሽነትን በማስፋትና የተቀላጠፈ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ጤንነቱ የተጠበቀ አምራች ዜጋ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የጤና ተቋማትን ደረጃ ማሻሻል ቁልፍ ተግባር ተደርጎ እየተተገበረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለዚህም ባለፉት ዓመታት በዞኑ የጤና ተቋማትን ተደራሽነት በማስፋት፣ ደረጃቸውን በማሻሻልና የህክምና ግብዓቶችን በማሟላት ለዜጎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በተደረገው ጥረት ውጤት ተመዝግቧል።

በቀጣይም አገልግሎቱን ይበልጥ በማዘመንና ዲጂታል በማድረግ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው፤ በሽታዎችን ቀድሞ በመከላከልና አክሞ በማዳን ላይ ያተኮረውን  የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።

በተለይም እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች ታግዘው እንዲወልዱ በማድረግ፣ በወሊድ ወቅት የሚያጋጥመውን የሞት ምጣኔ ለመቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግንባታ ላይ ከነበሩ 80 ጤና ተቋማት ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውም  አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

"አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ጭምር በማስደገፍና የውስጥ ግብዓት በማሟላት ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው" ያሉት ደግሞ የወግዲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሁሴን ሙሉጌታ ናቸው።

በአዲሱ በጀት ዓመትም የህብረተሰቡን ጤንነት በመጠበቅ አምራች ዜጋ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የጠቀሱት።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ አስተዳደር፣ የሆስፒታልና የጤና ተቋማት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም