በሀረሪ ክልል በትምህርት ዘመኑ የበለጠ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል በትምህርት ዘመኑ የበለጠ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ የመማር ማስተማር ስራ ተጀምሯል
ሀረር፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፡- በሀረሪ ክልል በ2019 የትምህርት ዘመን የበለጠ ስኬታማ ለመሆን የሚያስችል ዝግጅት ተደርጎ የመማር ማስተማር ስራ መጀመሩን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ነገዎ ገለጹ።
በክልሉ የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረ ሲሆን ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱ ተመላክቷል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ጌቱ ነገዎ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ በ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራን ለማሳካት በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በዚህም የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ "በትምህርት ለትውልድ" መርሃ ግብር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎችና በግብአት የማሟላት ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
የመማር ማስተማር ስራውን ለማሳካትም ትምህርት ቤቶችን ውብና ማራኪ የማድረግ፣ የመምህራንን አቅም የማሳደግና መሰል ተግባራት መከናወናቸውንም ጠቅሰዋል።
በትምህርት ቤቶች በ6ኛ፣ በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል የተማሪዎች ውጤት የታየን መሻሻል ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ተግባራት እንደሚከናወኑ አመላክተዋል።
በክልሉ በትምህርት ዘመኑ ከ91ሺህ በላይ ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ጠቁመው ለዚህም በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩን ገልፀዋል።
በክረምቱ ወራት ለተማሪዎች የማጠናከርያ ትምህርት ከመስጠት ጎን ለጎን ትምህርት ቤቱን ለማመር ማስተማር ስራ ዝግጁ በማድረግ ሀላፊነታቸውን ሲወጡ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የራስ መኮንን መጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዘኛ መምህርት ጠጅነሽ ለማ ናቸው።
በ2019 የትምህርት ዘመንም ለተማሪዎች አስፈላጊውን እውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ባለፈው የትምህርት ዘመን ጠንክራ በመስራቷ በጥሩ ውጤት ማለፏን የተናገረችው ደግሞ የራስ መኮንን ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ኤልዳን ሃይማኖት ናት።
ባለፈው አመት የነበራትን ዝግጁነት አጠናክራ በማስቀጠል ዘንድሮም የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደምትተጋ አመላክታለች።
የልጆቻቸውን ትምህርት አቀባበል ክትትል እንዲሚያደርጉ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሀረገወይን ሲሳይ እና አቶ አንዷለም አሸናፊ ናቸው።
በ2018 የትምህርት ዘመን ከትምህርት ቤት እና መምህራን ጋር ተቀራርበው በመስራታቸው የልጆቻቸው ውጤት እንዲሻሻል ማድረጉን አስታውሰዋል።
ዘንድሮው ከአምናው የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የጀመሩትን የተቀናጀ ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።