ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የሕልውና ጥያቄ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ጠንካራ መሰረት ያለው የሕልውና ጥያቄ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ ገለጹ።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን በሴራ ማጣት በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክስና በወደብ አገልግሎት የገቢና ወጪ ንግድ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ ይገኛል።

በየዓመቱም በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሬ እንድትከፍል በማስገደድ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትና እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው።

ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የሀገርን ተፈጥሯዊ፣ መልክዓ ምድራዊ፣ ስትራቴጂካዊና ሕጋዊ የባሕር በር ባለቤትነት ለማስመለስ ያነሱትን ጥያቄ ምክንያታዊነት ያጎላዋል።

ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በባሕር ላይ የሎጂስቲክስና ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ጠንካራ አቅም የገነባች ሀገር ናት።

በባሕር ላይ የንግድ መስመር፣ የሎጂስቲክስና ትራንስፖርት እንቅስቃሴም በትላልቅ መርከቦች፣ ብቁ የመርከብ ካፒቴኖችና በዳበረ መዋቅር የሚከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያን አቅም የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት የሚያስቆጭ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ይህም በባሕር ላይ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ስትጠቀምባቸው ከነበሩት የቀይ ባሕር ሉዓላዊ ወደቦቿ እንድትገለል የተፈጸመባት ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያሳደረባት መሆኑን ገልጸዋል።

የባሕር በር አለመኖሩም ኢትዮጵያን በወደብ ኪራይ፣ በሸቀጦች የወጪና ገቢ እንቅስቃሴ መዘገየት በመፍጠርና ቀጥተኛ ተፅዕኖ በማሳደር የኢኮኖሚ ዕድገትን እየጎተተ መሆኑን አስረድተዋል።

የባሕር በር ባለቤትነትም በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የወደብ አገልግሎት የሚያጋጥሙ ተፅዕኖዎችን በማስቀረትና የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠን ለዜጎች የሕይወት መሻሻል መሠረት መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በወደብ አገልግሎት የሚያጋጥሙ የትራንዚት መጨናነቅን፣ የገቢና ወጪ ምርት መዘግየትንና የወደብ ኪራይን ለማስቀረት ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።

የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በሚደረገው ጥረትም ሁሉም ዜጋ በትብብርና በንቁ ተሳትፎ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም