ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየፈታ ነው 

ድሬዳዋ ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ መደጋገፍና መረዳዳት ባህልን በማጎልበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተገለጸ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኻሊድ መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ90 ሺ በላይ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ14 ዘርፎች የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በአገልግሎቱ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ማዕድ ማጋራት፣ የደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና የሰላም እሴት ግንባታ እንዲሁም የተማሪዎች የትምህርት ግብአቶች ማሰባሰብ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በነዚሁ ዘርፎች እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት ከ250 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የፌደራል እና የአስተዳደሩ ሴክተር ተቋማትን በማስተባበርም 250 አዳዲስ የአረጋዊያን ቤቶች  እየተገነቡ መሆናቸውን  ጠቁመው እስካሁንም ከ100 በላይ ቤቶች ተጠናቀው መተላለፋቸውን ጠቅሰዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ እየታደሱ ከሚገኙት 150 ቤቶች መካከልም 80ዎቹ ተጠናቀው ለአረጋዊያኑ  መተላለፋቸውን አመልክተዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የእርስ በርስ መደጋገፍና መረዳዳትን በማጎልበት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ አይነተኛ ሚና እያበረከተ  መሆኑን ተናግረዋል።

ተግባሩ ጠንካራ መተሳሰብን በመፍጠር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን  ለማቃለል መሰረት በመጣሉ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ቤት የተገነባላቸው ወገኖችም፤  የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ  ቀደም ሲል ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአስቸጋሪ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩበትን ሁኔታ መቀየሩን አስረድተዋል።

ማህበራዊ ድጋፉ ችግራቸውን ከማቃለሉ በላይ አስታዋሽ ወገን እንዳላቸው በተግባር የተረዱበት በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም