የደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ረገድ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ረገድ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው
ሀዋሳ ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ):- የደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ የዜጎች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ደን ልማት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የደን ልማትና ማህበረሰብን ያሳተፈ የሰደድ እሳት ቃጠሎን መከላከል ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በወንዶ ገነት ደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር ሞቱማ ቶሌራ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን የደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የልማት ስራውን ማከናወኑ እንዳለ ሆኖ ለውድመት የሚዳርገውን የሰደድ እሳት አደጋ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል።
የሰደድ እሳት አደጋ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ ስጋትና የደን ውድመት መንስኤ መሆኑን ጠቅሰው አሳታፊ በሆነ መልኩ መከላከል አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ዜጎችን ያሳተፈ የመከላከል ስልት እየዳበረ መሆኑን ገልጸው በቀጣይነት ይበልጥ የተቀናጀ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የደን ልማትና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድ የዜጎች ጠንካራ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የደን ልማት ባህል ጥሩ መሻሻል እየታየበትና ውጤትም እየተመዘገበበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ ባለፉት ስምንት ዓመታት እንደ ሀገር የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን አንስተው የዩኒቨርሲቲውም አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለአረንጓዴ አሻራ ልማት መሳካት የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማፍለቅና በማሰራጨት የሀገር ሃብት እንዲሆኑ ማድረግ ስለመቻሉ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በዘርፉ ለልማት የሚሰጠውን ትኩረት ያክል በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም በሰደድ እሳት ሊከሰት የሚችል ውድመትን መከላከል አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የወንዶ ገነት የደንና ተፈጥሮ ኮሌጅ ዲን ተሻለ ወልደአማኑኤል (ዶ/ር)፤ ለደን ሃብት ልማት በሚሰጠው ትኩረት ልክ የመጠበቅና እንክብካቤ ስራ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በደን ሃብት ላይ ሊደርስ የሚችልን የሰደድ እሳት አደጋ ለመከላከል በጥናትና በምርምር የታገዘ የመከላከል ስልት መቀየስ ይገባል ብለዋል።
በዚህ ረገድ ኮሌጁ የድርሻውን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው አደጋና ውድመትን በመከላከል ሂደቱ የባለድርሻ አካላትና የዜጎች ጠንካራ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።