በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ውጤታማ ትውልድ የማፍራቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ውጤታማ ትውልድ የማፍራቱ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ድሬደዋ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ የትምህርት ፍትሃዊ ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በላቀ ደረጃ በማስቀጠል ውጤታማ ትውልድ የማፍራቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማሳደግ የመማር ማስተማሩን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም በክረምት ወራት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በህዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ አዳዲስ የቅደመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ትምህርት ቤቶችን ማደስና ግቢን በማሳመር ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ የማድረግ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ግንባታቸውን በመጠናቀቅ ደረጃ የሚገኙ ተጨማሪ ስምንት አዳዲስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችንም አገልግሎት ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግርዋል።
በተጨማሪም ዲጂታል የመማር ማስተማር ሂደትን ለማላቅ የስልጠና እና የኮምፒውተሮች እንዲሁም የቤተ ሙከራ እና የቤተ መፃሕፍት ግብአቶች የማሟላት ስራ መከናወኑን ገልፀዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በአስተዳደሩ የተመዘገበውን የተሻለ ውጤት በማስቀጠል ብቁ ትውልድ የማፍራቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ባለፉት አመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑት ተግባራት ብቁ እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት መቻሉን የተናገሩት ደግሞ የሳቢያን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር ኤጀታ መኮንን ናቸው።
በክረምት ወራት የመምህራን አቅም ግንባታ እና የትምህርት ግብአቶች ማሟላት ስራ በስፋት በመሰራቱ ዘንድሮም የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያግዙ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
የምስራቅ ጀግኖች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ፍሬህይወት ታደሰ በበኩላቸው፤ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በተግባር የታገዘ ትምህርት ለህፃናት መስጠት ተጀምሯል ብለዋል።
ወላጆች ከትምህርት ቤቶች ጋር ያላቸውን ትስስርና ድጋፍ በማጠናከር ልጆቻቸው የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የገለፁት ደግሞ የተማሪ ወላጅ ሰይፉ ታደሰ (ዶ/ር) ናቸው።