ቀጥታ፡

በትምህርት ዘመኑ ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀም ተዘጋጅተናል 

ጅግጅጋ ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ትምህርታቸውን በትኩረት ለመከታተል ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን በጅግጅጋ የሼክ አብዲሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ገለጹ።

በሶማሌ ክልል የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራው በሁሉም ወረዳዎች እና ዞኖች ተጀምሯል።

በየዓመቱ የትምህርት ዘመን ሲጀመር ተማሪዎች፣ መምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ አዲሱን የትምህርት ዘመን በብቃት ለመጀመር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን ያደርጋሉ። 

በተለይም በ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ ፈተናዎችና ለቀጣይ የከፍተኛ ትምህርት ዝግጅት የሚያደርጉበት ወቅት በመሆኑ፣ የጊዜ አጠቃቀምና የትምህርት ትኩረት ለውጤታማነታቸው ወሳኝ ድርሻ አለው።

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው የሼክ አብዲሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም በጥራትና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ተማሪዎቹ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለተሻለ ውጤት እንዲበቁ የማዘጋጀት ስራዎች ሲሰራ የቆየ ተቋም ነው።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በጅግጅጋ ከተማ የሚገኘው የሼክ አብዲሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በአዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን በንቃት በመከታተል ውጤታማ ለመሆን ሙሉ ዝግጅት አድርገዋል።


 

ከተማሪዎቹ መካከል የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዋ ኒምኦ ሀሰን እንደገለጸችው፤ በትምህርት ዘመኑ ስኬታማና ውጤታማ ለመሆን ጊዜዋን በአግባቡ ለመጠቀም ዝግጁነቷን አረጋግጣለች።

በተጨማሪም በትምህርት ዘመኑ ትምህርቷን በትጋት በመከታተል የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ አገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ሙሉ ዝግጅት ማድረጓን ተናግራለች።


 

ሌላኛዋ ተማሪ እስራ አብዲ ዩሱፍ በበኩሏ፤ ትምህርቷን በንቃት ለመከታተልና ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

በተጨማሪም በትምህርት ዘመኑ በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን የማጠናከሪያ ትምህርቶችን ለመከታተል ሙሉ ዝግጅት ማድረጓን ገልጻለች።

የሼክ አብዲሰላም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አብዱልቃድር አብድራህማን በበኩላቸው፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን የትምህርት ቤቱ አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።


 

በትምህርት ቤቱ የመማር ማስተማር ሂደቱ ምቹ እንዲሆን የመማሪያ ክፍሎችንና የቤተ-መጻሕፍት አገልግሎትን ማዘጋጀትን ጨምሮ የማጠናከሪያ ትምህርት ስልጠናዎችና ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶች ልማት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ መታን በበኩላቸው፤ በክልሉ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት የተለያዩ የማንቂያና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን በመግለጽ፣ የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራ በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።


 

ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትም በክረምቱ ወራት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን በመጥቀስ፤ ትምህርት ቤቶችና መምህራን ለዚሁ ተግባር ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም