በተደመረ አቅምና በተቀናጀ ጥረት በሁሉም ሴክተሮች ለላቀ ስኬት በጋራ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በተደመረ አቅምና በተቀናጀ ጥረት በሁሉም ሴክተሮች ለላቀ ስኬት በጋራ መስራት ይገባል
ደብረ ማርቆስ ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦በተደመረ አቅምና በተቀናጀ ጥረት በሁሉም ሴክተሮች ለላቀ ስኬት በጋራ መስራት ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
በአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር "አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት" በሚል መሪ ሃሳብ የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ የትውውቅ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፤ በየደረጃው ያሉ አመራሮች መልካም ጅምሮችን አጠናክሮ በመቀጠል ለላቀ ውጤት ለመብቃት መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ለዚህም የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ ጠንካራ ትብብርና ትጋት ወሳኝ መሆኑን አንስተው ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም ስራ መስራት ይገባናል ብለዋል።
በተለይም የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የግብርና ልማትን ማስፋፋትና ምርታማነትን ማሳደግ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የክልሉን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ከተረጅነት የመውጣት ጥረትን ማሳካት አስፈላጊ መሆኑንም ርእሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
በተደመረ አቅምና በተቀናጀ ጥረት በተያዘው በጀት ዓመት በሁሉም ሴክተሮች ለላቀ ስኬት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም ለማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት ልዩ ትኩረት በመስጠት የተሟላ መሰረተ ልማት እንዲኖራቸውና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋትና ለዲጂታል አገልግሎት ትኩረት በመስጠትም ዘመናዊና የተፋጠነ አገልግሎት የመስጠት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።