በባሕርዳር ከተማ ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በባሕርዳር ከተማ ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል
ባህር ዳር ፤መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦በአዲሱ በጀት ዓመት ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዘመነ አሰፋ እንደገለጹት፤ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አንዱ የልማት ቁልፍ ተግባር ተደርጎ እየተሠራበት ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ61 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው የገለጹት።
የሥራ ዕድሉ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በሌሎች ዕድገት ተኮር ዘርፎች እንዲሁም በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ዘርፎች መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ወደ ሥራ ለሚገቡ ወገኖች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር፣ ከ230 ሄክታር በላይ መሬት፣ 124 ሼዶችና 124 ኮንቴይነሮችን ማመቻቸቱን ነው የተናገሩት።
በበጀት ዓመቱ 2 ሺህ 767 አዳዲስ ኢንተርፕራይዞችን በዶሮ፣ በወተት፣ በጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ዘርፎች በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት መታቀዱንም ጠቁመዋል።
የ"እናንዬ፣ አስማረችና ጓደኞቻቸው" የዓሣ ምርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ እናንዬ ታምሩ በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት 70 አባላትን በማቀፍ በዓሣ ልማት ዘርፍ ተደራጅተው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ማኅበራቸው በቀን እስከ 20 ኪሎ ግራም ዓሣ በማዘጋጀትና ለገበያ በማቅረብ አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የ"አዲሴና ምሕረት" የዶሮ እርባታ ሽርክና ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አዲሴ አብረሃም፤ በየዙሩ 1 ሺህ ጫጩቶችን በማስመጣትና በማሳደግ ለተጠቃሚዎች እያሰራጩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ዘርፉ አዋጭ በመሆኑ ሌሎች ወጣቶችም ተደራጅተው ወደ ሥራ በመግባት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመለወጥ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት ከ55 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ከዕቅድ በላይ ስኬታማ አፈጻጸም ማስመዝገቡን መግለጹ ይታወሳል።