የኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት የሀገሪቱን የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አቅም በተግባር ያሳየ ስኬት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት የሀገሪቱን የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አቅም በተግባር ያሳየ ስኬት ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን በዓለም ጤና ድርጅት የደረጃ አንድ ቋሚ ድንገተኛ ሕክምና ቡድን እውቅና ማግኘቱ የሀገሪቱን የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አቅም ያሳየ ትልቅ ስኬት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውን የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን እውቅና ያገኘች ሲሆን የእውቅና አሰጣጡ ይፋዊ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን የደረጃ አንድ ቋሚ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን በመሆን ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ የሀገሪቱን የድንገተኛ አደጋ ዝግጁነትና ምላሽ አቅም የሚያሳይ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
ለሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎችና የተለያዩ ወረርሽኞች ቀድሞ መዘጋጀት የጤና ሥርዓቱን ጽናት፣ ዘላቂነትና የጤና ሉዓላዊነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም ነው ጨምረው የተናገሩት።
እውቅናው በረጅም ጊዜ የተደረገ ዝግጅት፣ ልምምድ፣ የባለሙያዎች ምርጫ እና የአጋር ተቋማት ድጋፍ ውጤት መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፣ የዓለም ጤና ድርጅት የደረጃ አንድ ቋሚ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን እውቅና መገኘቱ የኢትዮጵያን የተቀናጀና ጠንካራ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አቅም የሚያሳይ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረት እና በድንገተኛ ሕክምና ቡድን በገነባችው አቅም ለዚህ ውጤት መብቃቷን አመልክተዋል።
የተገኘው እውቅና የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሂደቱን የሚያስቀጥል ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው፣ የድንገተኛ ሕክምና ቡድኑን አቅም ወደ ክልሎች ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው፣ የዓለም ጤና ድርጅት እውቅና የኢትዮጵያ የድንገተኛ አደጋ ዝግጁነትና የጤና ሥርዓቱ ጽናት በዓለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ተገምግሞ የተረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከሀገር ውስጥ ምላሽ ባሻገር በዓለም አቀፍ የጋራ የድንገተኛ ሕክምና ሥራ ላይ ለመሳተፍ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ቺሳካ ኮሶሎ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ያገኘችው ዓለም አቀፍ እውቅና የዓመታት ሀገራዊ አመራር፣ ኢንቨስትመንት፣ የአቅም ግንባታና የአጋርነት ውጤት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የድንገተኛ ሕክምና ቡድን በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ውስጥ ዓለም አቀፍ እውቅና ካገኙ የሲቪል የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች መካከል የመጀመሪያው መሆኑንና የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርቶችን ሙሉ በሙሉ ያሟላ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
እውቅናው የስኬት መዳረሻ ሳይሆን የዝግጁነት፣ የሥልጠና፣ የልምምድና የፈጣን ምላሽ አቅምን በቀጣይነት ማጠናከር የሚጠይቅ ኃላፊነት መሆኑን ጨምረው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የድንገተኛ ሕክምና አቅም ግንባታ ልምዷን ለማካፈል ዕድል እንደሚፈጥርም ነው ተወካዩ የተናገሩት።