የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የአዲሱ ትውልድ ቁርጠኝነት ትልቅ መሠረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የአዲሱ ትውልድ ቁርጠኝነት ትልቅ መሠረት ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የአዲሱ ትውልድ ቁርጠኝነት ትልቅ መሠረት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ መጀመርን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት በመላው ሀገሪቱ ለሚገኙ ተማሪዎች አዲሱ የትምህርት ዘመን ስኬታማ እንዲሆን ተመኝተዋል።
ወጣቱ ትውልድ ለኢትዮጵያ ትልቁ ሀብቷ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እያንዳንዱ ተማሪ ለላቀ እውቀት በትጋትና ጉጉት ትምህርቱን መከታተልና ለጥሩ ውጤት በጽናት መትጋት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
አዲሱ ትዉልድ የሀገሪቱን የወደፊት ዕድል መቅረጽ በሚያስችሉ ክህሎቶች እንዲገነባም አበረታተዋል።
በሃገሪቱ ዛሬ እየተተገበሩ የሚገኙት በርካታ የልማት ሥራዎች የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ በመሆናቸው ትዉልዱ የዚህ ቀጣይ ዕድል ተጠቃሚ እና ባለአደራ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ታላቅ የስልጣኔ ታሪክ ወደፊት ለማስቀጠል የአዲሱ ትውልድ ቁርጠኝነት ትልቅ መሠረት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ብቁ እና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመምህራኖች ትጋትና መሰጠት መሰረታዊ ምሰሶ መሆኑንም አንስተዋል።
ተማሪዎችን ማነቃቃት፣ አቅማቸውን ማውጣት፣ እንዲሁም ነገ ተፎካካሪ ሆነው እንዲወጡ የሚያስችሏቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና እሴቶችን የማስታጠቅ አደራን እንዲያስቀጥሉም በትህትና አሳስበዋል።
በትምህርት ዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም ስኬታማ እና ፍሬያማ የትምህርት ዘመን እንዲሆን የበኩላቸዉን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።