ቀጥታ፡

የግብርና ምርት እሴት ሰንሰለትን ለማሻሻል ትብብርና የፖሊሲ ማዕቀፍ መተግበር ይገባል - ኢጋድ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፡- በአባል ሀገራት ቀጣና የግብርና ምርትን ለማሻሻልና እሴት ለመጨመር ትብብርን በማጠናከርና ሊያግባባ የሚችል የጋራ የፖሊሲ ማዕቀፍ መተግበር እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።

ኢጋድ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2026 እስከ 2035 ለ10 ዓመታት የሚተገብረውን የቀጣናው የግብርና ምርት የምግብ ሥርዓት ኢንቨስትመንት ዕቅድ የባለሙያዎች ግምገማና በሚኒስትሮች የማጽደቅ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።

የኢጋድ የምግብ ሥርዓት ግንባታ አቅም ፕሮግራም አስተባባሪ ሰናይት ረጋሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የኢጋድ ቀጣና ሀገራት እንደ ጎርፍ፣ ድርቅና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎችን በተደጋጋሚ የሚያስተናግዱ ናቸው።

የአፍሪካ መሪዎች እ.ኤ.አ. በ2025 በዩጋንዳ ካምፓላ ተገናኝተው የምግብ ሥርዓት ግንባታ አቅም ስምምነት ሰነድ በመፈራረም ለትግበራው ቁርጠኝነታቸውን ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።


 

በዚህም በአህጉር፣ በቀጣናና በሀገር ደረጃ ገቢራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መደረጉን ገልጸው፤ የኢጋድ የግብርና ምርት የምግብ ሥርዓት ኢንቨስትመንት የ10 ዓመት ዕቅድ የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ከምግብ ዋስትና ጋር የተያያዙ ችግሮች በሀገር ደረጃ ብቻ የሚፈቱ አለመሆናቸውን ገልጸው፤ የ10 ዓመት ዕቅዱ የሀገራትን የጋራ ትብብር እንደሚያጠናክር ብለዋል።

ለአብነት የበረሃ አንበጣ በቀጣናው ቢከሰት አንድ ሀገር ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይችልም ያሉት አስተባባሪዋ፤ የቀጣናው ሀገራት በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔና እርምጃ መውሰድ የሚችሉበትን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ዕቅዱ ሀገራት በተናጠል ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ከሚወስዷቸው የመፍትሔ አማራጮች ባለፈ ትብብራቸውን ማጠናከርና የዕውቀት ሽግግር መፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የኢጋድ የግብርና ምርት የምግብ ሥርዓት ኢንቨስትመንት ዕቅድ የግብርና ምርትን ከማሳደግ ባለፈ እሴት መጨመር የሚቻልበትን አቅም መገንባት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ ድንበር ተሻጋሪ በሽታዎችን በጋራ መከላከል የሚችሉበት ሥርዓት እንዲዘረጋ ድጋፍ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የቀጣናው ሀገራት የሚስማሙበትን እና ግብራዊ ሊያደርጉት የሚችለውን የጋራ ቀጣናዊ የፖሊሲ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪና የአፍሪካ ልማት ፕሮግራም ተወካይ ዜና ሀብተወልድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከአፍሪካና ከቀጣናው ሀገራት ጋር የተናበበ ዕቅድ በመተግበር በአርዓያነት የሚጠቀስ ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል።

በሌማት ትሩፋት፣ በስንዴ ልማት እንዲሁም አሁን በስፋት ግብራዊ በተደረገው የሩዝ ልማት ተጨባጭ ለውጥ መገኘቱን ገልጸዋል።

ግብርና የአፍሪካ የልማት ሞተር መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይሄንን ታሳቢ ያደረገ የግብርና ዕመርታ አምጥታለች ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ በካምፓላ ስምምነትና በኢጋድ የ10 ዓመት የኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ በመመስረት የቀጣይ 10 ዓመት የተናበበ ዕቅድ በማውጣት ግብራዊ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

ኢጋድ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለቀጣናው ሀገራት የምግብ ዋስትና መረጋገጥና በሽታ መከላከል ሥርዓት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ቀጣናዊ ትብብርና ተቋማዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም