ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሐረር፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የክልሉ አመራሮች በክረምቱ ወራት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ አከናውነዋል።

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

በችግኝ ተከላው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የመከላከያና ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ አርሶ አደሮች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውም እንዲሁ።

በዛሬው እለትም ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች 'በሃኪም' ጋራ በመገኘት የተከሏቸውን ችግኞች ውሃ የማጠጣት እና የመንከባከብ ሥራ አከናውነዋል።

በክልሉ በክረምቱ ወራት የተተከሉት ችግኞች ወደ ዛፍነት እስኪቀየሩ ድረስ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንዳሉት፣ በክልሉ በክረምቱ ወቅት የተተከሉት ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

በአሁኑ ወቅትም በተለይ የተተከሉ ችግኞች ለሚፈለገው ዓላማ እንዲበቁ እየሰሩ የሚገኙ አካላትን አበረታተዋል።

በቀጣይም ችግኞቹን ውሃ በማጠጣትና በመኮትኮት እንዲፀድቁ ማድረግ እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።

ከዚህ በተጨማሪ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የሃኪም ጋራ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት የስራ እንቅስቃሴን ተዘዋዉረው ተመልክተዋል።


 

የፕሮጀክቱ ስራ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም