ቀጥታ፡

በተለያየ መንገድ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቅርሶች እንዲመለሱ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):-በተለያየ መንገድ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከአሜሪካ የተመለሱና የተረከባቸውን 17 የብራና መጻሕፍት ለሰባት የተለያዩ ተቋማት አስረክቧል።


 

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንዳሉት፤ ለቅርስ ማስመለስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በተለያዩ ጊዜያትና መንገዶች ወጥተው የነበሩ ቅርሶች እንዲመለሱ ተደርገዋል።


 

ዛሬ ወደ ሀገር የተመለሱት 17 የብራና መጻሕፍት የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያን በቅርበት የሚያውቁት ጄራልድ ዌይነር የተባሉ ግለሰብ የብራና መጻሕፍቱን በአሜሪካ ከሚገኙ የጥንታዊ ዕቃዎች ገበያ በተለያዩ ጊዜያት በመግዛት በግል ስብስበው ማቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

ጄራልድ ዌይነር ከሞቱ በኋላ ባለቤታቸው ባርበራ ዌይነር ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አለባቸው በማለታቸውና በተደረገው ንግግር ቅርሶቹን ማስመለስ ተችሏል ብለዋል። 

እነዚህ ከ13ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ዕድሜ ያላቸው 17 የብራና መጻሕፍት ለሰባት ተቋማት መሰራጨታቸውንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ሌሎች ቅርሶችን የማስመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አመልክተዋል። 

በተጨማሪም በአቡዳቢ ለጨረታ የወጣውን የአፄ ቴዎድሮስ ብራና ከጨረታ እንዲወጣና ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ ወጥተው የነበሩ የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶችና መጻሕፍት ከተለያዩ አካላት ተሰብስበው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።


 

በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ67 በላይ ቅርሶችን ማስመለስ መቻሉንና ዛሬ የተመለሱት የብራና መጻሕፍት የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የእውቀት ታሪክ ምስክሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶክተር አሉላ ፓንክርስት በበኩላቸው፤ እነዚህ 17 የብራና መጻሕፍት በአንድ ላይ መመለሳቸው ሁነቱን የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል። 

 

ቅርሱን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ የመጣው ቡድን ወኪል ፕሮፌሰር ስቲቭ ዴላማተር በበኩላቸው፤ እያንዳንዱ የጽሑፍ ቅጅ የራሱ የሆነ ታሪካዊ እሴት ያለው በመሆኑ፣ እነዚህን ውድ ቅርሶች አክብሮት ባለው መልኩ መመለስ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም