የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስትራቴጂካዊ አቅምና ሙያዊ ብቃት ለመላው አፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስትራቴጂካዊ አቅምና ሙያዊ ብቃት ለመላው አፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት አስርት ዓመታት የገነባው ስትራቴጂካዊ ዲሲፕሊን፣የቴክኒክ ልህቀት እና የላቀ ሙያዊ የብቃት ደረጃ ለመላው አፍሪካ አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ገለጹ።
የአየር መንገዱ ስኬት በመንግስት ባለቤትነት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በሙያዊ ስነምግባርና በገለልተኝነት በመመራቱ ጭምር መሆኑን የቀድሞው ዲፕሎማት ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ተቋሙ በቴክኒክ አቅምና በሰው ኃይል ልማት ላይ ያደረገው ሰፊ ኢንቨስትመንት አሁን ላይ ለደረሰበት ዝና እና ስኬት ቁልፍ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል።
አየር መንገዱ ጠንካራ ስትራቴጂ ያለው እና የላቀ የቴክኒክ አቅም የተጎናጸፈ መሆኑን ገልጸው የአውሮፓ አየር መንገዶች አብራሪዎቻቸውን በአዲስ አበባ በሚገኙ ማሰልጠኛዎች (ሲሚውሌተር) ልምምድ እንዲያደርጉ እንደሚልኩ አንስተዋል።
የተቋሙ መካኒኮችም በዓለም ምርጥ ከሆኑት ተርታ እንደሚመደቡ ጠቅሰው መንገደኞች ሁልጊዜም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተመራጭ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ በረራዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጠው በነበሩበት አስቸጋሪ ወቅት አየር መንገዱ የላቀ ሙያዊ ብቃት ማሳየቱን ናጊ አስታውሰዋል።
በወቅቱ የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ በሚያገለግሉበት ወቅት፣ ሌሎች አየር ማረፊያዎች በረራቸውን ባቋረጡበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት አሜሪካ ዜጎቿን ከአፍሪካ ለማስወጣት አየር መንገዱን በስፋት ስትጠቀም እንደነበር በማውሳት የአየር መንገዱን ጽናትና አይበገሬነት አንስተዋል።
የቢሾፍቱን ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ያደነቁ ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ የኢኮኖሚና የአቪዬሽን መሪነት እንድትቀጥል ይህ ፕሮጀክት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ የረጅም ጊዜ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አርቆ አሳቢነት የተሞላበት አካሄድ ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ እጅግ ከፍ ያለ ቦታ ላይ መሆኗ ለአንዳንድ አውሮፕላኖች ማረፍና መነሳት አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህም የፕሮጀክቱን ስትራቴጂካዊ ፋይዳ የጎላ የሚያደርገው መሆኑን ተናግረዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት 12.5 ቢሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፤ ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በቢሾፍቱ ከተማ እየተገነባ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ይበልጥ የአፍሪካ ግዙፍ የአቪዬሽን ማዕከል የሚያደርጋት ነው።
የኢትዮጵያን አየር መንገድ ስኬት ከረጅም ጊዜ የተቋም ጽናትና ኢንቨስትመንት ጋር የሚቆራኝ ነው ብለዋል።
የቴክኒክ ባለሙያዎች ብቃት፣ስትራቴጂካዊ አስተዳደር እና የመሰረተ ልማት መቀናጀት እንዲሁም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና የዓለም አቀፍ ትስስር እድገት አየር መንገዱ ያለውን አህጉራዊ ሚና ይበልጥ እንደሚያሳድገው አመልክተዋል።