ቀጥታ፡

ጤናማ ዜጋ አምራች ሀገር፤ የመደመር መንግሥት የጤና ፖሊሲ ትሩፋት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ነገን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተገበረችው አዲስ የጤና ፖሊሲ የመደመር መንግስት ቃልን በተግባር የመተርጎም ብቃትን ከሚያመላክቱ ትሩፋቶች መካከል ተጠቃሽ ነው። 

የመደመር መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት ትኩረት ከሰጠባቸው ዘርፎች መካከል ማህበራዊ ልማት ዘርፉ ተጠቃሽ ነው። 

በዚሀ ዘርፍ ከሚመደቡት መካከል ደግሞ የጤና ዘርፉ ተጠቃሽ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትሃዊ እና ተደራሽ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚችልበትን ዕድል ለመፍጠር የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግን ጨምሮ የጤና መሰረተ ልማት ግንባታ እና የሰለጠነ የጤና ባለሙያ አቅም ግንባታ ላይ ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል።

ቅድሚያ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገውን የጤና ፖሊሲ በመከለስ ለአክሞ ማዳንም ትኩረት እንዲሰጥ መደረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግስት ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በርካታ ሆስፒታሎች ተገንብተው ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉንና በዚህም በዘርፉ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።


 

የመደመር መንግስት የህብረተሰቡ ጤና በተሟላ መልኩ ሲጠበቅ ምርታማነት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አዎንታዊ ሚና በሚገባ በመረዳት ከጤና መሰረተ ልማት ባሻገር ህብረተሰቡ አስቀድሞ ጤናውን ለሚጠብቅባቸው መሰረተ ልማቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። 

ለዚህ ነው በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራ የሚገኘው ይህ የመንግስት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የግል ዘርፉም የህብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ እና ለፖሊሲው ውጤታማነት በኩሉን ድርሻ መወጣት የሚችልበት ዕድል ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የተገበረችው አዲስ የጤና ፖሊሲ እና በዘርፉ የወሰደቻቸው ውጤታማ እርምጃዎች አይበገሬ የጤና ስርዓት መዘርጋት አስችሏታል። 

መንግስት ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለሀገር እድገትና ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ ባለፉት ዓመታት ውጤታማ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰዱ የጤና ቱሪዝም ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ስትከተል የቆየችው በሽታ መከላከል ላይ ብቻ ያተኮረው የጤና ፖሊሲ፣ በጤና አገልግሎት አሰጣጥና የተቋማት ግንባታ እንዲሁም በዘርፉ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም አንጻር ክፍተት ይታይበት ስለነበር ውጤታማነቱ ላይ የራሱን ተግዳሮት ደቅኖ ቆይቷል። 

የመደመር መንግስት የጤናው ዘርፍ ፖሊሲ ምሉዕ የሚሆነው በሽታ መከላከል ላይ ብቻ በማተኮር ሳይሆን አክሞ ማዳንንም የፖሊሲው የትኩረት ማዕከል ማድረግ ሲቻል መሆኑን በማመነ ፖሊሲው ይህንን ባካተተ መልኩ እንዲሻሻል አድርጓል።

በተጨማሪም አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ ለጤና መሰረተ ልማት ግንባታ ለአካታች የጤና አገልግሎት ለጤና ፋይናንስ እና ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤታማነት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ በመንግስትም ሆነ በግል ዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ያካተቱ በርካታ የጤና መሰረተ ልማቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ተደርጓል።


 

ለዚህም ይመስላል በአዲስ አበባ ከተማ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማዘመን፣ በማስፋፋትና ጥራቱን በማሳደግ ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ መሳሪያዎችን በማስገባት የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መናገራቸው።

በጤው ዘርፍ የአገልግሎትን ጥራት፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ቁለፍ ጉዳይ ነው። የመደመር መንግስት እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ለአዳዲስ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ግንባታ እንዲሁም ለነባሮቹ የጤና ተቋማት የማሻሻያ እና የማዘመን ተግባራት በመከናወናቸው በአገልግሎት ጥራት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ አንጻር ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የህክምና ተቋማትን በዘመናዊ የህክምና ግብዓት ማደራጀትና አቅማቸውን ማሳደግ ፍትሃዊ እና ተደራሽ የሆነ እንዲሁም አስተማማኝ የህክምና አገልግሎት በመስጠት የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ርዕይ ለማሳካት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በጤና ዘርፍ የነበሩ ክፍተቶችን መቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የሚገልጹት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህም የመንግስት የጤና ተቋማት ቁጥርና የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ ማደጉን በመጥቀስ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ሽፋን እና የዜጎች ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ለዘርፉ ዕድገት ጥሩ ማሳያ ነው።


 

ባለፉት ስምንት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት እምርታ መመዝገቡን የመድሃኒት፣ የክትባት እና የህክምና ግብዓቶች ምርት አቅርቦት እና ቁጥጥር መጨመሩን እንዲሁም በጤና ፋይናንስ ስርዓት ላይ የተመዘገበውን ለውጥ በማሳያነት ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይ በጤናው ዘርፍ የተከሰቱ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችንና በዘርፉ የተስተዋሉ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችላለች። 

በዚህም የወረርሽኝ ልየታ እና ቁጥጥር፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ የጤና ባለሙያዎችን ማብቃትና ቁጥራቸውን ማሳደግ፣ የዲጂታል ጤና እና በዘርፉ የተከናወኑ ልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት በጤና ዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች መሆናቸውን ሚኒስትሯ መጥቀሳቸው ለተፈጠረው አቅም ጥሩ ምሳሌ ነው።

የመደመር መንግስት ለማህበራዊ ልማት በተለይም ለጤናው ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ምክንያት በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። 

እነዚህ በዘርፉ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለጤና ዲፕሎማሲ ዘርፍ እመርታ አበርክቷቸው ከፍተኛ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ የገለጹ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያ የተለያዩ የዘርፉ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን እንድታስተናግድ ተመራጭ እንዳደረጋት እና ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተመርጣ ዓለም አቀፍ የጤና ድርድሮችንና ንግግሮችን እንድትመራ እንዳስቻላትም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም