ቀጥታ፡

በመደመር መንግሥት በሳል ዲፕሎማሲ ዓቅም የተመዘገበ የብሪክስ ድል

ኢትዮጵያ በረጅም የዲፕሎማሲ ታሪኳ የገነባችውን ልምድ ከዘመኑ ዓለም አቀፍ ለውጦች ጋር በማጣጣም፣ብሔራዊ ጥቅሟን በማስቀደምና ከተለያዩ የዓለም ኃይሎች ጋር አጋርነቷን በማስፋት በሳል የውጭ ግንኙነት አካሄድ እየተከተለች ትገኛለች።

የዚህ አካሄድ ጉልህ ውጤት ማሳያ ደግሞ ኢትዮጵያ የብሪክስን ጥምረት መቀላቀሏ ነው። ይህ ስኬት ግን የጥምረቱ አባል በመሆኗ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። ኢትዮጵያ በመድረኩ የራሷን ብሔራዊ አጀንዳ በጥምረቱ የጋራ አቋም እንዲያገኝ ማድረግ መቻሏ ዋናው የዲፕሎማሲ ውጤት ሆኗል።

ይህን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ በመቅረጽና በመምራት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚና ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ የብሪክስ ቡድንን ለመቀላቀል ፍላጎቷን በመግለጽ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ቀጥተኛ እና ታሪካዊ የዲፕሎማሲ መሪነት በነሐሴ 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ በነበረው 15ተኛው የብሪክስ ጉባዔ ላይ ጥያቄዋ ተቀባይነትን አግኝቶ፣ በጥር 2016 ዓ.ም በይፋ መቀላቀሏ ይታወሳል፡፡ አሁን ላይ ከ11 የብሪክስ አባል ሀገራት ውስጥ አንዷ ሆና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የራሷን ጉልህ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በተለዋዋጭ የዓለም ሥርዓት ውስጥ ከአንድ የኃይል ጎራ ጋር ብቻ ሳትወግን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የትብብር መድረኮች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠር እንዳለባት ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ዓለም አቀፍ የትብብርና የተፅዕኖ አድማሷን እያሰፋች ነው። የብሪክስ አባልነትም ከዚህ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ የመነጨ ነው።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ውስጥ መግባቷ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጥቅም የሚያመጣውን አቅም በመለየት፣ አጀንዳውን ከኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተሳሰረ ስትራቴጂያዊ የዕይታ ለውጥ ውጤት ነው።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን ከዲፕሎማሲያዊ ጥረት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቻይና፣ ከሩሲያ ከሕንድና ከሌሎች የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር ባደረጉት ከፍተኛ የመሪዎች ዲፕሎማሲና ኢትዮጵያ ለዓለም ያበረከተችውን ታሪካዊ ሚና በቀጥታ ማስረዳታቸው ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ኢትዮጵያ በብሪክስ ያላት የነቃ ተሳትፎና የድል የጉዞ አሁንም ቀጥሏል። ከመስከረም 2 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ በህንድ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳዎቿን አሰምታለች። ብሔራዊ መሻቷን ገልጻለች። ድሎችን ተቀዳጅታለች።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር ለችግሮች የማይበገር ፅኑ ሥርዓት እየገነባች መሆኗን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በምግብ ሉዓላዊነት በስንዴ ምርት ያስመዘገበችውን ስኬት፣ በጤና፣ በዲጂታል ሽግግርና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ያላትን አቅም በማሳደግ ራሷን የመቻልና ለወደፊት የመዘጋጀት አቅሟን እያጠናከረች መሆኗን ጠቁመዋል። ‎

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጉዳይ እያደገ ካለው ገዙፍ ኢኮኖሚዋና የህዝቧ ፍላጎት አኳያ አጣዳፊ ምላሽ የሚሻ ስትራቴጂያዊ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ መሆኑን በግልጽ አቅርበዋል።

ይህ ኢትዮጵያ የራሷን ወሳኝ ብሔራዊ ጥያቄዎች በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ሁሉ በተቀናጀ መልኩ ለማስገንዘብና ምላሽ እንዲያገኙ የምትከተለውን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ፍሬያማነት ያሳያል።

‎የመሪዎቹ ጉባኤ 140 የጋራ አቋሞችን የያዘ የኒው ዴልሂ መግለጫ በማውጣት ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያም በድል ተመልሳለች።

‎‎በብሪክስ ኒው ዴልሂ የአቋም መግለጫ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት ጥምረቱ በጽኑ እንደሚደግፍ በድጋሚ አረጋግጧል።


 

በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ብቸኛ እጩ በመሆን ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የሚደረገውን ጥረት በጽኑ እንደሚደግፍም አመላክቷል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32 ለማዘጋጀት የጀመረችውን ተነሳሽነትና ዝግጅት እንደሚደግፉ የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች በጋራ መግለጫቸው አረጋግጠዋል።

‎በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህነዱ የብሪክስ ጉባኤ ከአባልና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን ያካሄዱ ሲሆን፤ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ መስኮችና በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች በጥልቀት መወያየታቸው ሌላኛው ስኬት ነው።

‌‎የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድልም ነው። በተያያዘም የብሪክስ አባል በመሆኗ አሁን ላይ ተሰሚነቷ ከማደጉም በላይ በፋይናንስ፣ ኢንቨስትመንት እና መሰል የዕድገት መሰረተ ልማት ትብብሮች ላይ አማራጮችን አበርክቶላታል።


 

ለዚህም ኢትዮጵያ የኒው ዴቨሎፕመንት ባንክን በአባልነት መቀላቀሏ ለሀገራዊ የልማት ፋይናንስ፣ ለመሠረተ ልማት ድጋፍ እና ለማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት የሚያስችላትና ከደቡብ ደቡብ የፋይናንስ ሥርዓቶች ጋር የሚኖራትን ትስስር የሚያጠናክር ነው።

ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም በተለያዩ የብሪክስ የወጣቶች ማዕቀፍ ውስጥ በስራ ፈጠራ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ ሳይንስ እና መሰል መስኮች ላይ በንቃት እየተሳተፉ የሚገኝ ሲሆን፣ እየተፈጠሩ በሚገኙ የኢንቨስትመንት እድሎችም በርካታ የስራ እድሎች እየተፈጠረለቸው ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ከአባል እና አጋር ሀገራቱ ወጣቶች ጋር ትስስር የመፍጠርና ልምድ ልውውጥ የማድረግ ዕድሎችን አስገኝቶላቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባንኩ የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ እንዲቋቋም ያላትን ዝግጁነት መግለጿም የብሪክስን አባልነት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ትስስር ለመቀየር ያላትን ፍላጎት ያሳያል።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ስኬታማ ጉዞ በዓለም አቀፍ ለውጥ መካከል በተለያዩ የትብብር መድረኮች በመሳተፍ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስገኘት በትጋትና በተፅዕኖ ፈጣሪነት እየሰራች መሆኗን ያሳያል።

ብሪክስ የኢትዮጵያ ጥያቄዎች የሚሰሙበት፣ አጋርነቶችን የምትገነባበት፣ ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ የምትፈጥርበት፣ አፍሪካን በመወከል አጀንዳዎቿን የምታራምድበት መድረክም ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም