ኢትዮጵያ ዘላቂና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይዋን ውጤታማ በሆነ መልኩ አጠናክራ ቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘላቂና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይዋን ውጤታማ በሆነ መልኩ አጠናክራ ቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ዘላቂና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ራዕይዋን ውጤታማ በሆነ መልኩ አጠናክራ መቀጠሏን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (Nordic Africa EV Summit) ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት አረንጓዴና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የልማት ስትራቴጂን በሀገራዊ የልማት ዕቅዷ ማዕከል አድርጋ እየሰራች ትገኛለች።
የአረንጓዴ አሻራ፣ የታዳሽ ኃይል ማስፋፋት፣ የአረንጓዴ ከተማ ልማት እና ዝቅተኛ የካርቦን ልቀት ያለው ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረት ኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫዋን ለመለወጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የሀገሪቱ የረጅም ጊዜ የአየር ንብረት ስትራቴጂ የትራንስፖርት ዘርፉን ከካርቦን ነፃ ማድረግን ዋነኛ መንገድ አድርጎ ማስቀመጡንም ጠቁመዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን፣ የሕዝብ ትራንስፖርትን፣ የአረንጓዴ ከተማ ኮሪደሮችን እና ንፁህ የትራንስፖርት ሥርዓቶችን ከታዳሽ ኃይል አቅም ጋር የማዋሃድ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
ይህ ጥረት ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን፣ የኃይል ደህንነት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪ ልማት እና የዜጎችን የኑሮ ጥራት የማሻሻል አጀንዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ ግንኙነት እና መሠረተ ልማት ክፍል ዳይሬክተር ሮበርት ታማ ሊሲንጌ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የመጠቀምና የማምረት አጠቃላይ አዝማሚያ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
አህጉሪቱ ኃይል በማመንጨት ላይ ብቻ ሳትወሰን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲሁም ወደ አውሮፓና እስያ ለመላክም መስራት እንዳለባት ገልጸው፤ ሀገራት ተሽከርካሪዎቹን ለማስገባት የሚያስችሉ ማበረታቻዎችንና የተሟላ ስነ-ምህዳር በመፍጠር ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የኖርዲክ-አፍሪካ ኢቪ ሳሚት ሮድ ቱ አፍሪካ የሀሳብ መሪ ሚከል ቤከር አከርቪክ እንደተናገሩት፤ ከተሞችን ከካርቦን ነፃና ንፁህ አየር እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚፈጠረው የልቀት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አሰራር መተግበር በኢኮኖሚ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢ ጥበቃም እውነተኛ ትራንስፎርሜሽን እንደሚያመጣ አስረድተዋል።