ቀጥታ፡

በሕብር የተሸመነ አንድነት፤ የኢትዮጵያ ጥንካሬ የወል እውነት

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):-በሕብር የተሸመነ አንድነት፤ የኢትዮጵያ ጥንካሬ የወል እውነት

የኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ግንባታ የታሪክ ምዕራፎች ከዜጎቿ በሕብር የተሸመነ አንድነት የሚመነጭ ነው።

በዚህ የረጅም ዘመናት የታሪክ ጉዞም የኢትዮጵያውያን ብዝኅ ማንነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች፣ ባሕሎችና ልዩ ልዩ እሴቶች በአንዲት የኢትዮጵያ ማዕቀፍ ሥር ተሳስረውና ተሰናስለው የዘለቁ ውድ ሀብቶች ናቸው።

የኢትዮጵያውያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተሸመነ እውነትም ከሀገር መለያነት ባሻገር በዜጎች መካከል ለዘመናት የተገነባ የጋራ ሕይወት ውጤት ነው።

በሕብር የተሸመነው ይህ ማኅበራዊ እሴት በልዩነት ውስጥ የእኛነት፣ በብዝሃነት ውስጥ የአንድነት፣ በተለያዩ ማንነቶች ውስጥ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት አሸብርቆ ይታያል።

ይህን የጋራ እውነት በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ ማሸጋገርም በራሱ መንገድ ብቻ የሚፈጸም አይደለም። የጋራ ታሪክ፣ እሴትና ሀገራዊ ምልክትን በማስተሳሰር አሰባሳቢና የጋራ ትርክትን መገንባትም ይጠይቃል።

የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ የተለያዩ ማንነቶችን ማጥፋት ሳይሆን፤ በልዩነቶች መካከል የጋራ እሴቶችን በማጉላት ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ መሰለፍ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው የአስተሳሰብ ውቅር ነው።

በዚህ ሂደት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የጋራ ታሪካቸውን በመረዳት፣ የጋራ እሴቶቻቸውን በማጎልበትና የጋራ የወደፊት ራዕይን በመጋራት ከእኔ ወደ እኛ የሚያመራ ሀገራዊ አስተሳሰብን ያጎለብታሉ።

ለዚህም ሀገራዊ ምክክር ጉልህ ሚና አለው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም ለዘመናት የተስተጋቡ የአለመግባባት ትርክቶችን በአሳታፊና አካታች የሃሳብ የበላይነት ለማረቅ ሁነኛ መሰረት ጥሏል።

የምክክር ጉባኤው ምክረ ሃሳብ ውጤቶችም የመቀራረብና የአንድነት መንፈስን በማጎናጸፍ ኢትዮጵያውያን ቀጣይነት ላለው ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የሚተባበሩበትን ታሪካዊ ዕድል ፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ምክክር ከእኔነት ወደ እኛነት ሀገራዊ ማዕቀፍ የሚያመራ ሁነኛ የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ መንገድ ነው ብለዋል።

የምክክር ጉባኤውም ለሀገርና ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የጋራ ሀገራዊ አስተሳሰብን ለማጠናከር መሰረት የሚጥል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የምክክር መድረኩም የታሪክን፣ የአጋጣሚንና የዕድልን ማዝለቀቅ ለፈለጉ ሰዎች፤ በዚያ ብዕርና ብራና ላይ ሀገርን የሚታደግ፣ የሚገነባና ለዘመናት የሚታወስ ታሪክ ለመጻፍ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ይህም ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የምክረ ሃሳብ ውጤቶች ከአንድ የምክክር መድረክ በላይ ለጋራ ሀገራዊ እሴትና የወደፊት ራዕይ ግንባታ ወሳኝ ዕድል የሚፈጥር ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ያመላክታል።

ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ አንድነትና ትብብር የጋራ ታሪክን ወደ የጋራ የወደፊት ራዕይ ለመለወጥ የሚያስችሏት በርካታ አጋጣሚዎችን ያሳለፈች ታላቅ ሀገር ናት። ከእነዚህ መካከል የዓድዋ ድል አንዱ ምልክት ነው።

የዓድዋ ድል በአንድ ዘመን በተፈጸመ ወረራ ላይ የተገኘ ወታደራዊ ድል ብቻ አይደለም። በሕብር የተሸመኑ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ሉዓላዊ ነጻነት ለማስጠበቅ በአንድ ዓላማ የተሰለፉበት የጋራ ታሪካዊ የወል እውነት ነው።

የዓድዋ ድል በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የደምና አጥንት መስዋዕትነት ደማቅ ቀለም ተሸምኖ የተጻፈ የነጻነት ታሪክ ነው።

በዚህ የታሪክ ገጽ የግል ልዩነቶቻቸውን በይደር የያዙ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ጥቅም ከግል ጥቅም በተሻገረ ዕይታ በመመልከት ከአራቱም ማዕዘናት ለጋራ ዓላማ ተሰልፈው ድልን የተጎናጸፉበት ክስተት ሆኗል።

ይህ የዓድዋ ትርክት ለዛሬው ትውልድ የሚያስተላልፈው ዋና መልዕክትም የሀገርን ጉዳይ በማስቀደም ለጋራ ዓላማ መሳካት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተሸመነ ሀገራዊ ትብብር ወሳኝ አቅም መሆኑን ነው።

የዓድዋ አርበኝነትን በልማት የትብብር መንፈስ የተላበሰው አዲሱ ትውልድም በጉባ ተራሮች ግርጌ በፈጸመው ታላቅ ገድል ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት የራሱን ታሪክ ጽፏል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫም በትብብር፣ በመደጋገፍና በዜጎች የጋራ ርብርብ የተገነባ መሆኑ የዘመኑና የቀጣይ ትውልድ የጋራ ሀገራዊ አሰባሳቢ ትርክት መገንቢያ ፕሮጀክት ለመሆን በቅቷል።

በፕሮጀክት ግንባታ ሂደትም የአራቱም ማዕዘናት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያላቸውን በማዋጣት በጋራ ተሰልፈዋል፤ የሀገር ጉዳይ ሲሆን የጋራ ዓላማ ልዩነት እንደማይገድባቸውም በተግባር አስመስክረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በትርክት መዛባት ምክንያት የበዙ ውድ ዋጋዎችን ስትከፍል መቆየቷን አስታውሰዋል።

በዚህም የመደመር መንግሥት የትናንት ቁርሾዎችን በንግግር፣ በውይይትና በምክክር መፍትሔ በመስጠት አሰባሳቢና የወል ትርክትን ለመገንባት የሚያስችል መሰረት መጣሉን አስገንዝበዋል።

ለዚህም እኩልነትን፣ አካታችነትንና አሳታፊነትን ማዕከል ያደረገ አሰባሳቢና የወል ትርክት እየተገነባ መሆኑን አጽንኦት የሰጡት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው፤ ንዑሳን፣ አካባቢያዊ፣ ተቋማዊና ሌሎች የትርክት ዓይነቶች የሰው ልጆች ጠባይና ተፈጥሯዊ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ንዑሳን ትርክቶችንም ሀገር እንደ ትምህርትና ፕሮጀክት በማድረግ ልታበረታታቸው አይገባም ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ፤ የሀገር መሰረታዊ ማዕከል የወል እውነት ነው ብለዋል።

በሀገር ደረጃ ሁሉንም የሚያስተሳስር የወል ትርክት ቀዳሚ ሊሆን እንደሚገባ ማስገንዘባቸውም አስተሳሳሪ ትርክት ግንባታ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አስረጂ ነው።

ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ ሕዝቦቿን በማስተሳሰር የወል ትርክት መገንባት የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ያስተናገደች ሀገር ናት።

ለዚህም ከሩቁ የዓድዋ ድልን፣ ከቅርቡ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህን ታሪካዊ አጋጣሚዎችም ለጋራ የወል ትርክት ግንባታ በመጠቀም ለዛሬ ብሎም ለነገ ሀገራዊ ራዕይ ስኬትና አንድነት አይተኬ ሚና አላቸው።

ለዚህም ነው የኢትዮጵያን የጋራ ታሪክና እሴቶች ወደ የጋራ የወደፊት ራዕይ ማሸጋገር፣ ብዝሃነትን እያከበሩ አንድነትን ማጠናከር የወል ትርክት ዋነኛ እሳቤ መሆኑን የሚያስረዱት አማካሪ ሚኒስትሩ።

ዓድዋ የነጻነት የጋራ ትርክት፤ ሕዳሴ ደግሞ የልማትና የራስ መተማመን የጋራ ትርክት ውጤት ሆኗል። ይህም የአንዱ ትውልድ ቅርስ የነጻነት እሴት ሲያስተላልፍ፣ ሌላው ደግሞ የዛሬውን ትውልድ በጋራ ራዕይ በማሰባሰብ የነገን የዕድገትና ብልፅግና ምኞት ተልሟል።

የመደመር እሳቤም በእኛነት መርህ ላይ ተመሥርቶ ብዝሃነትን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ የጋራ ብልፅግና አቅም በመመልከት፣ የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ አድርጎ እየሰራበት ነው።

በዚህም የዓድዋ ድል ይህንን ታሪክ ያስተማረን ሲሆን፣ የሕዳሴ ግድብ ደግሞ በዘመናችን በተግባር የተገለጠ የአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ የወል እውነት ማዕከልነትን ቀርጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም