በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ ተጀምሯል
አምቦ/መቱ/ነቀምቴ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራው በይፋ ተጀምሯል።
በክልሉ በሁሉም ደረጃዎች ከቅድመ-መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከ10 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማስገባት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል።
የአዲስ እና ነባር ተማሪዎች ምዝገባ ከነሐሴ 2018 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፣ ተማሪዎች ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ወደ ክፍል እንዲገቡም በሁሉም አካባቢ ጥሪ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።
በምዕራብ ሸዋ፣ በኢሉ አባቦር ዞኖች እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማም ለአዲሱ የትምህርት ዘመን አስፈላጊው ቁሳቁስ፣ የመማሪያ ክፍሎች እና የመምህራን ዝግጅት ተጠናቆ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ሲሆን፣ የመማር ማስተማር ሂደቱም በተሳካ ሁኔታ መቀጠሉ ተገልጿል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኙ 2 ሺህ 296 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ 858 ሺህ 856 ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ በትምህርት ገበታቸው መገኘታቸውን የዞኑ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንዲራ ጋላና ገልጸዋል።
ሥራው ከመምህራን፣ ወላጆችና አመራሮች ጋር በተደረገ መግባባት መጀመሩና የቁሳቁስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎችም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ የመቱ ከተማ እና የኢሉባቦር ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች አቶ አዳሙ ሀብቴ እና አቶ አያሌው ዘውዴ፤ ተማሪዎች በጥሩ ተነሳሽነት ትምህርት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
በኢሉባቦር ዞን እና በመቱ ከተማ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ባሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት የተጀመረ ሲሆን፣ በመቱ ከተማ 22 ሺህ 124 እንዲሁም በዞኑ ወረዳዎች ከ211 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ተናግረዋል።
በመቱ ከተማ በትምህርት ገበታ ላይ ከተገኙት ተማሪዎች መካከል የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሚኪያስ ጫላ ትምህርቱን በከፍተኛ ተነሳሽነት መከታተል መጀመሩን ተናግሯል።
ዘንድሮ 6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተነ ተፈታኝ በመሆኑ ከአሁኑ ተግቶ በማጥናት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀቱን ገልጿል።
ተማሪ አማኑኤል ግርማ በበኩሉ ትምህርቱን በአግባቡ በመከታተል ተወዳዳሪ ለመሆን ከወዲሁ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
በተመሳሳይ ዜና የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍቃዱ ተስጋራ (ዶ/ር) በከተማው በሚገኙ 169 ትምህርት ቤቶች ከ78 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ወደ ሥራ ገብተናል ብለዋል።
ለትምህርት ቤት ኃላፊዎችና መምህራን ሥልጠና መስጠትን ጨምሮ ተጨማሪ ክፍሎችን የመገንባትና የመጠገን ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ውስጥ 11 በመቶው ማለፋቸውን ተጠቅሶ፣ በዘመኑ የትምህርት ጥራትን ማሻሻልና ውጤትን ማሳደግ ዋና ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው የ7ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ሳሙኤል ግርማ ትምህርቱን በአግባቡ በመከታተል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀቱን ገልጿል።
ሌላኛዋ ተማሪ ለሊሴ ኦፍገአ፤ ከጅምሩ ጊዜዋን በአግባቡ በመጠቀመ መምህራኖቿን በመከታተልና በማጥናት ወጤታማ ለመሆን ማቀዷን ተናግራለች።
የየአካባቢዎቹ የትምህርት ኃላፊዎችና ተማሪዎችም ዓመቱን በስኬት ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።