ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት እያደረገ ነው

ሰመራ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):-የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን ከፍ በማድረግ የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያና የኢትዮጵያ ስነ ልክ ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ 200 ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የአምስት አቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ  ስነ ስርአት አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ቅድስት ስጦታው በወቅቱ እንደገለጹት በመደጋገፍና በመተጋገዝ ለትውልድ የሚሆን የበጎ ተግባራትን ማከናውን ይገባል። 


 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አብሮነትን ከፍ በማድረግ የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ስነ ልክ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆሰ በበኩላቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለትውልድ የሚሆን በጎ ተግባራት የማከናወን ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።


 

በዚህም ተቋማቱ በጋራ በመሆን በሰመራ ከተማ ለአምስት አቅመ ደካሞች የቤት ግንባታ ለማካሄድ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም  ለ200 ተማሪዎች ቦርሳ፣ ደብተርና እስክሪብቶ ያካተተ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የአፋር ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመተባበር ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የታየበት መሆኑን ገልፀዋል።


 

የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አህመድኑር ሳሊም በበኩላቸው በከተማው የሚገነቡት የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች የመደጋገፍ እሴትን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

 በተቋማቱ ለተደረገው የበጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም