ቀጥታ፡

የመማር ማስተማር ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መጀመሩ ጊዜያችንን ተጠቅመን ውጤታማ እንድንሆን ያግዘናል

ሀዋሳ ፤መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፡- የመማር ማስተማር ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መጀመሩ ጊዜያችንን በተገቢው ተጠቅመን ውጤታማ እንድንሆን ያግዘናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ተማሪዎች ገለጹ።

በሲዳማ ክልል የ2019 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራው ዛሬ ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ የመማር ማስተማር ስራውን በሀዋሳ ታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።


 

ለኢዜአ አስተያየታቸው የሰጡ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የአመቱ ትምህርት በወጣለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መጀመሩ ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የታቦር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ዳኛቸው ደግፌ በመጀሪያው ቀን ትምህርት ቤት መገኘት የተለየ ስሜት እንዳለው ተናግሯል፡፡

አመቱ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስድበት ዓመት መሆኑን ተከትሎ ባለፉት የክረምት ወራት በማጠናከሪያ ትምህርት ላይ መቆየቱን ገልጾ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችለውን አቅም አጎልብቶ ትምህርት መጀመሩን ገልጿል፡፡

የትምህርት መርሃ ግብሩ በመስከረም ወር መጀመሪዎቹ ቀናት እንዲጀመር መወሰኑ የአመቱን ትምህርት በተቀመጠለት ጊዜ ከማጠናቀቅ ባለፈ በቂ ዝግጅት ለማድረግ የሚያግዝ በመሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ገዳም እንየው በበኩሏ የትምህርት የመጀመሪያ ቀን ተማሪዎች በጉጉት እንደሚጠብቁት ገልጻ ሃገር አቀፍ ፈተና የምትፈተንበት ዓመት መሆኑ ደግሞ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጻለች፡፡

የአመቱ ትምህርት መጀመሪያ መስከረም ወር በበዓላት ታጅቦ የሚመጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም የትምህርት መርሃ ግብሩን በጊዜ የመጀመር ችግር መኖሩን አስታውሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይሄ መቀየሩን ተናግራለች፡፡


 

በዚህም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተቀመጠላቸው መርሃግብር መሰረት አጠናቀው በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን ገልጻለች፡፡

በትምህርት ቤቱ በክረምት ወራት የተደረገላትን የማጠናከሪያ ትምህርት ጨምሮ ግቢውን ለማመር ማስተማር ምቹ የማድረግ ስራ የትምህርት ዓመቱን በብሩህ ተስፋ እንድጀምር አስችሎኛል ብላለች፡፡

የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ወንዳቸው ሙለታ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ በአመቱ 5ሺህ 600 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር መርሃ ግብሩን ዛሬ በይፋ ጀምሯል ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱን ለመማር ማስተማር ዝግጁ የማድረጉ ስራ በተቀናጀ መልኩ መከናወኑን የጠቀሱት ርዕሰ መምህሩ የዓመቱን የትምህርት ጊዜ በስኬት ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡንና ዘንድሮም የማሳለፍ ምጣኔን ለማሳደግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ትምህርት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ በማስጀመሪያው መርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ የትምህርት ዓመት ስኬት የሚጀምረው በመጀመሪያው ቀን ትምህርት ቤት በመገኘት ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የተማሪዎችን ውጤታማነት የሚያረጋግጡ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው በተለይም የተማሪ መጽሐፍ ጥመርታ ካለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ዘመኑ በክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ተማሪዎችን ለማስተማር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ክልል አቀፉ የትምህርት ማስጀመሪያ መርሃግብሩ በይፋ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም