ቀጥታ፡

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):- 22ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.አ.አ በ2029 በኬንያ ናይሮቢ ይደረጋል።

የዓለም አትሌቲክስ ምክር ቤት በሀንጋሪ ቡዳፔስት ባካሄደው ስብስባ የ2029 እና የ2031 ውድድር አስተናጋጅ ከተሞችን ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት እ.አ.አ በ2029 22ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያ እንዲካሄድ ምክር ቤቱ ወስኗል።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ በውድድሩ የ43 ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ናይሮቢ የ2029ን ውድድር ማስተናገዷ ለአፍሪካ አትሌቲክስ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚከፍት ነው።

ኬንያ ከዚህ ቀደም የዓለም ከ18 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮናዎችን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነውን «ኪፕ ኬይኖ ክላሲክ» ውድድር ማስተናገዷ ለዚህ ስኬት ትልቅ መሠረት ሆኗታል።

የጀርመኗ ከተማ ሙኒክ እ.አ.አ በ2031 የሚካሄደው 23ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንድታስናግድ ተመርጣለች።

ሙኒክ ሻምፒዮናውን ስታስተናግድ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ውሳኔውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ አስተናጋጅ ከተሞችን ለመምረጥ የተደረገው ሂደት አጓጊ እንደነበር ገልጸዋል።

ናይሮቢ እና ሙኒክ ለአህጉራቱ ልዩ ዕድሎችን የሚያመጡ አሳማኝ እቅዶችን በማቅረባቸው ሊመረጡ መቻላቸውን ተናግረዋል።

21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.አ.አ በ2027 በቻይና ቤጂንግ ይካሄዳል።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.አ.አ በ1983 በፊንላንድ ሄልሲንኪ የተጀመረ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም