ቀጥታ፡

በሸገር ከተማ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የ2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ ተጀምሯል

ሸገር፣ መስከረም 5/2019(ኢዜአ)፡- በሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የ2019 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራ በይፋ መጀመሩ ተገለጸ።

በሸገር ከተማ ደረጃ በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ ተካሂዷል። 

በዚህም ተማሪዎች በሙሉ ዝግጅት ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው የተመለሱ ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን ቁሳቁስና የመማሪያ ክፍሎች አሟልተው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።

የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈጠና በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤  ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ዘንድሮም ለማስቀጠል በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።

በተለይም የተማሪዎችን ውጤት ለማሳደግና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አንስተዋል። 


 

በከተማው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ከመተግበር ባለፈ፣ የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበልና  ውጤት ለማሻሻል የሚያስችሉ የክትትልና ድጋፍ ስልቶች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል።

በትምህርት ዘመኑ አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የተመለሱ ሲሆን፣ የመማር ማስተማር ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

በተጨማሪም መምህራን የተሻለ የማስተማር ዘዴን በመጠቀም የተማሪዎችን ውጤታማነት እንዲያሳድጉና የትምህርት ቤቶች አካባቢ ለትምህርት ተስማሚና ምቹ እንዲሆኑ መደረጉን አመልክተዋል።


 

የመማር ማስተማሩን ሂደት በተሳካ ሁኔታ ለማስቀጠል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በከተማው በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከ333 ሺህ በላይ ተማሪዎች  ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ አስታውቀዋል።

በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ወላጆች እና የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም