ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ከአሜሪካ የተመለሱና የተረከባቸውን 17 የብራና መጻሕፍት ለሰባት የተለያዩ ተቋማት አስረከበ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ከአሜሪካ የተመለሱና የተረከባቸውን 17 የብራና መጻሕፍት ለሰባት የተለያዩ ተቋማት አስረክቧል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ ለቅርስ ማስመለስ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራው ስራ በርካታ ቅርሶችን ማስመለስ ተችሏል። 

ዛሬ የሀገር ውድ ቅርሶች ወደ አገር የተመለሱበት ታላቅ ቀን መሆኑን ጠቁመው ፤ ሌሎች ቅርሶችን የማስመለስ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይም በርካታ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ አመልክተዋል። 


 

አያይዘውም ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ጥረት ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ ወጥተው የነበሩ የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶችና መጻሕፍት ከተለያዩ አካላት ተሰብስበው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። 

በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ67 በላይ ቅርሶችን ወደ አገር ማስመለስ በመቻሉ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ገልፀዋል።

ዛሬ የተመለሱት የብራና መጻሕፍት የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የእውቀት ታሪክ ምስክሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።


 

የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸው፤ እነዚህ 17 የብራና መጻሕፍት በአንድ ላይ መመለሳቸው ሁነቱን የተለየ እንደሚያደርገው ገልፀው፣ ለተመለሱት ቅርሶች ልዩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ቡድኖች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የተመለሱትን የብራና መጻሕፍት የተረከቡት ሰባት ተቋማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ ማኅበረ ቅዱሳን እና የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ እና ሃይሌ ሚናስ አካዳሚ ናቸው፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም