በአዲስ አበባ በ2018 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በ2018 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በ2018 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተከናወኑ በርካታ ቅንጅታዊ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አበራ ባይሳ ገለጹ።
የትራፊክ ቁጥጥር ዋና መምሪያው የ2019 የትምህርት ዘመን መጀመርን በማስመልከት "በእኔ የመንገድ አጠቃቀም ስህተት የትራፊክ አደጋ መከሰት ይብቃ" በሚል መሪ ሃሳብ በአራት ኪሎ ፕላዛ የመንገድ ደህንነት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
የትራፊክ ቁጥጥር ዋና መምሪያ ኃላፊው ኮማንደር አበራ ባይሳ በዚሁ ወቅት፤ በ2018 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
ይህንን ውጤታማነት በበለጠ ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ስራዎቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው በመንገድ አጠቃቀም ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ የንቅናቄው ዋና አላማ እንደሆነ ገልጸዋል።
እያንዳንዱ የመንገድ ተጠቃሚ ለትራፊክ አደጋ መከላከል ድርሻ እንዳለውና ይህንኑ ሀላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አክለዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ለእግረኞች ቅድሚያ የመስጠት አስፈላጊነትን በውል በመገንዘብ ማሽከርከር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት በነበረው የጋራ ቅንጅትና አሰራር ምክንያት የሞት፣ የከባድ እና የቀላል አደጋዎችን መጠን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ መቻሉንም አመላክተዋል፡፡
ይህ ውጤት የተመዘገበው የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥና የትራፊክ አደጋዎችን ለመከላከል ማህበረሰቡን እና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ስራዎች በመሰራታቸው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በ2019 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋን ከዚህም በላቀ መጠን ለመቀነስ የማህበረሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የከተማዋን የመንገድ ደህንነት የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚና የስራና ክህሎት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አብዲ ሙሉነህ በበኩላቸው፤ በክፍለ ከተማው የተገነቡ ጥራታቸውን የጠበቁ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ለአካባቢው የትራፊክ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ምቾት ፈጥረዋል ብለዋል።
በተለይም በአራት ኪሎ ፕላዛ የተገነባው ሰፊ እና ዘመናዊ የእግረኞች መንገድ ማኅበረሰቡ የነበረውን የቆየ የመንገድ አጠቃቀም ባህል እንዲያሻሽል ትልቅ ሚና መጫወቱን አመላክተዋል።
ይህ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማት እግረኞች ያለ ስጋት በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ በኩል የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡