በክልሉ የትምህርት ተሳትፎና ጥራት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ተሳትፎና ጥራት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሀረር፤ መስከረም 5/2019(ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል የትምህርት ተሳትፎና ጥራት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
በክልሉ በ2018 በትምህርት ዘርፉ ለተገኘው አመርቂ ውጤት የእውቅና ፕሮግራም ተካሂዷል።
"ጥራት ያለው ትምህርት ለሀገር ብልጽግና " በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ እንዳሉት በክልሉ የተማሪዎች ትምህርት ተሳትፎና ጥራት ለማስጠበቅ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ለአብነትም በክልሉ በ12ኛ፣ በ8ኛ እና በ6ኛ ክፍል ሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎች በየትምህርት ዘመኑ ውጤቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለውጤቱ መሻሻልም የትምህርት አመራሩ፣ የመምህራን፣ የተማሪዎች ወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ሥራ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመው ቀሪ ስራዎች እንዳሉም አንስተዋል።
በዘንድሮው አመትም የተማሪ ውጤትን በማሻሻል ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ቅንጅታዊ ተግባራት እንደሚጠናከሩ አመላክተዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የተከናወኑ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልና ግብዓት የማሟላት ተግባራት ለዘርፉ ውጤታማነት አስተዋጽዎ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ ናቸው።
በዚህም 12ኛ፣ 8ኛና በ6ኛ ክፍል የተማሪ የማለፍያ ምጣኔ በየዓመቱ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በተለይ በ6ኛ እና 8ኛ ክፍል 100 በመቶ ማሳለፍ የሚችሉ ትምህርት ቤቶች በከተማም ሆነ በገጠር መፈጠራቸውን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን መፍታት ላይ በቅንጅት የመስራቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩም በትምህርት ዘርፉ አበረታች ውጤት ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች፣ ወረዳዎች፣ የትምህርት አመራሮች፣ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሌሎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
እንዲሁም በ12ኛ ክፍል ከ500 ነጥብ በላይ ያመጡ ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማት ከእለቱ ክብር እንግዳ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተበርክቶላቸዋል።