ቀጥታ፡

አኩቴክ ዲያግኖስቲክ የህክምና ቱሪዝም ማዕከልነት ግብ ለማሳካት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦ አኩቴክ ዲያግኖስቲክ ሀገሪቱን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የአኩቴክ ዲያግኖስቲክ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ ታደሰ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በቅርቡ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሥራ እንቅስቃሴ መመልከታቸው ይታወሳል።


 

በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ አኩቴክ (ACCU-TECH) ዲያግኖስቲክ ላቦራቶሪ የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እና ለዘርፉ ልዩ መለያ እና አቅም ነው።

ዘመናዊው ላቦራቶሪ በአንድ ጊዜ በርካታ ናሙናዎችን በመቀበል ለተወሰነ ጊዜ ሳምፕሎችን በጥንቃቄ ማቆየት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።

የአኩቴክ ዲያግኖስቲክ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ስያሜው "አኩ" ትክክለኛነትን እና "ቴክ" ቴክኖሎጂን የሚወክል ሲሆን፣ የሚጠቀማቸው ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች የምርመራ ውጤቶች ጥራት እንዲኖራቸው ያስችላሉ።

ይህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ላቦራቶሪ ወደ ውጭ ሀገር ተልከው ይሠሩ የነበሩ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።


 

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ከሪቲና ፋርማሲዩቲካል ጋር በመተባበር የተቋቋመው ላቦራቶሪ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ አውቶሜትድ የሆነ ነው ብለዋል።

ላቦራቶሪው በምርመራ ሂደቶች ላይ የሚታዩ የውጤት መዘግየቶችንና የውጭ ምንዛሬ ወጪዎችን ለማስቀረት ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም እስከ 68 በመቶ የሚደርሱ ስህተቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አንስተው፣ አሁን ያለው ሲስተም ይህንን ዲጂታላይዝ በማድረግ ስህተቱን ወደ ዜሮ እንደሚያወርደው አስረድተዋል።

ላቦራቶሪው በርካታ ናሙናዎችን በአንድ ጊዜ የመመርመር ብቃት ያለው ከመሆኑ ባሻገር ናሙናዎችን በጥንቃቄ የሚያቆይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ማሽኖቹ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ጋር የተገናኙ በመሆናቸው ሥራን በቀላሉና በፍጥነት እንዲያከናውኑ ማስቻሉን አንስተዋል።

በቀጣይም አገልግሎቱን በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ በድሮን ናሙና መሰብሰብ የሚያስችል ተግባር ለማከናወን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ላብራቶሪው ሀገሪቱን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካትም ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም