ብቃት ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረፅ የተጀመሩ የትምህርት ዘርፍ የለውጥ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብቃት ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረፅ የተጀመሩ የትምህርት ዘርፍ የለውጥ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ ብቃት ያለውና አገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረፅ የተጀመሩ የለውጥ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት ማሳየት መጀመራቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።
ሚኒስትሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማሻሻል በተጀመረው ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ እና የትምህርት ስርዓት ሪፎርሞች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የለውጡ ዋና ዓላማ ከቅድመ-መደበኛ፣ ከ1ኛ ደረጃ እና ከ2ኛ ደረጃ ጀምሮ በራስ መተማመን ያለው፣ ጥራትና ሙሉ አቅም ያለው አዲስ ትውልድ መገንባት መሆኑንም አብራርተዋል።
የሪፎርሙ ውጤት በሂደት እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የትምህርት ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱንና ትክክለኛ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በአገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተደረገው የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም የተማሪዎችን ውጤትና አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለው መምጣቱን አበክረው ገልፀዋል።
በቀጣይም ተማሪዎች ከዚሁ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችንም ጭምር እንዲያስተምሩ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
ይህ የተቀናጀ የትምህርት ስርዓት ተጠናክሮ ሲቀጥል፣ በፅኑ መሰረት ላይ የቆመና የነገዋን አገር በብቃት መሸከም የሚችል አዲስ ትውልድ ማፍራት እንደሚያስችል ታምኖበታል ብለዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወነው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ አማካኝነት በገንዘብና በአይነት በርካታ ሀብት ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት መሰብሰቡን አንስተዋል።
ይህ ንቅናቄ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡና የወላጆች ንቁ ተሳትፎ የታየበት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም ወደ 17 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፤ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ዕድሳት ተደርጎላቸው ለ2019 በጀት ዓመት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በመገንባታቸው የተማሪዎችን መጨናነቅ መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማስጠበቅ ስራዎች በዘላቂነት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ያላቸው ተነሳሽነትና ክትትል መጨመሩ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልፀዋል።