ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):- በታንዛንያ አዘጋጅነት የሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ዛሬ ጅማሮውን ያገኛል።
በውድድሩ ላይ ዘጠኝ ሀገራት በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ታንዛንያ እና ሩዋንዳ ጋር ተደልድሏል።
በአሜሪካዊው ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው ብሔራዊ ቡድን መስከረም 7 ከሩዋንዳ እና መስከረም 9 ከአዘጋጇ ታንዛንያ ጋር ይጫወታል።
በምድብ ሁለት ዩጋንዳ፣ ሱዳን እና ጅቡቲ እንዲሁም በምድብ ሶስት ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ እና ብሩንዲ ይገኛሉ።
ዛሬ በውድድሩ መክፈቻ ቀን በምድብ አንድ አዘጋጇ ታንዛንያ ከሩዋንዳ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በምድብ ሁለት ዩጋንዳ ከጅቡቲ ከቀኑ ስምንት ሰዓት፣ በምድብ ሶስት ደቡብ ሱዳን ከብሩንዲ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቡድኑ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የሚገባው ከምድቡ አንደኛ ወይም ከሶስቱ አጠቃላይ ምድቦች ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ካጠናቀቀ ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በጋና እ.አ.አ በ2027 ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣሪያ ውድድሩ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ይኖርበታል።
ብሔራዊ ቡድኑ በጋና በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑ ካለፈ እና ግማሽ ፍጻሜ መድረስ ከቻለ በዛው ዓመት በአዘርባጃን እና ኡዝቤኪስታን ጣምራ አዘጋጅነት ለሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማለፉን ያረጋግጣል።
የሴካፋ ዞን ማጣሪያ እስከ መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።