ቀጥታ፡

ኤፕስዊች ታውን ከአርሰናል እና ሊቨርፑል ከቶተንሃም ሆትስፐርስ: የካራባኦ ካፕ የሶስተኛ ዙር ጨዋታዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ):- ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የእንግሊዝ ካራባኦ ካፕ የሶስተኛ ዙር መርሐ ግብር በዚህ ሳምንትም ቀጥሎ ይካሄዳል።

ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ምሽት አራት ሰዓት ላይ ኤፕስዊች ታውን ከአርሰናል በፖርትማን ሮድ ይጫወታሉ።

በሁለተኛ ዙር የውድድሩ መርሐ ግብር ኤፕስዊች ታውን ሌስተር ሲቲን 3 ለ 1 ረትቷል።

ተጋጣሚው አርሰናል የካራባኦ ካፕ ጉዞውን ዛሬ በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።

ሁለቱ ክለቦች በካራባኦ ካፕ ሲገናኙ የአሁኑ ለስድስተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ኤፕስዊች በአንዱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

የሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ያነሳው እ.አ.አ በ1993 ነው።

መድፈኞቹ ባለፈው የውድድር ዓመት ለፍጻሜ ደርሰው በማንችስተር ሲቲ የ2 ለ 0 ሽንፈት ማስተናገዳቸው ይታወሳል።

የኤፕስዊች ታውን ትልቁ ውጤት በሶስት አጋጣሚዎች ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰባቸው ናቸው።

ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው እ.አ.አ በ2011 ሲሆን ከዛሬው ተጋጣሚው አርሰናል ጋር ለፍጻሜ ለማለፍ ተፋልሟል። ይሁንና ሽንፈት አስተናግዶ ወደ ፍጻሜ መድረስ አልቻለም።




በሌላኛው መርሐ ግብር ሊቨርፑል ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ቶተንሃም ሆትስፐርስን ያስተናግዳል።

ሊቨርፑል 10 ጊዜ የካራባኦ ዋንጫን በማንሳት ስኬታማው ክለብ ነው። ተጋጣሚው ቶተንሃም አራት ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በውድድሩ ላይ አምስት ጊዜ ተገናኝተው በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናቸው በቀሪው ጨዋታ ነጥብ አቻ ተለያይተዋል።

ለመጨረሻ ጊዜ እ.አ.አ በ2025 በግማሽ ፍጻሜ ተገናኝተው ቶተንሃም በመጀመሪያው ጨዋታ 1-0 ቢያሸንፍም፣ በመልሱ ጨዋታ ሊቨርፑል አንፊልድ ላይ 4-0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፎ (በድምር ውጤት 4-1) ወደ ፍጻሜው አልፏል።

በሌሎች የሶስተኛ ዙር መርሐ ግብሮች ዌስትሃም ዩናይትድ ከፉልሃም እና ፒተርቦሮው ከባርንስሌይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሬዲንግ ከብሬንትፎርድ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በሰሌክት ካር ሊዚንግ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም