ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም፣ አረንጓዴ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም፣ አረንጓዴ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም፣ አረንጓዴ እና ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓትን ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የኖርዲክ-አፍሪካ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ (Nordic Africa EV Summit) ጉባኤ ላይ ነው።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት አረንጓዴና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የልማት ስትራቴጂን በሀገራዊ የልማት ዕቅዷ ማዕከል አድርጋ እየሰራች ትገኛለች።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የታዳሽ ኃይል ማስፋፋትና ዝቅተኛ ካርቦን ያለው ኢኮኖሚ የመገንባት ጥረት የዚሁ ቁርጠኝነት ማሳያ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የትራንስፖርት ዘርፉን ከካርቦን ነፃ ማድረግ ለዘላቂ ኢኮኖሚ ግንባታ ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት አንዱ መሆኑን አመልክተው፤ ሀገሪቱ ይህንን ውሳኔ ወደ ተግባር ለመቀየር የኤሌክትሪክ ህዝብ ትራንስፖርት፣ የአረንጓዴ ከተሞች ኮሪደር እና የፅዱ አየር ትራንስፖርት ስርዓትን ከታዳሽ ኃይል አቅሟ ጋር አስተስስራ እየገነባች እንደሆነ ገልፀዋል።
የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ሽግግር ለአካባቢ ጥበቃ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን፣ ለኃይል ዋስትና፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራና ለዜጎች የህይወት ጥራት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
ተሽከርካሪዎችን ብቻ ወደ ሀገር ማስገባት የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ምህዳርን ሙሉ በሙሉ ሊፈጥር እንደማይችል አመልክተው፤ የተሟላ ውጤት ለማስመዝገብ መሰረተ ልማቶችና አሰራሮች ማሟላት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚህም የቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋትና የዲጂታል አሰራርን መዘርጋት፣ ሁለንተናዊ ስታንዳርዶችን ማዘጋጀት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት (ኢንጂነሮችንና ቴክኒሻኖችን ማሰልጠን) እንዲሁም የባትሪዎችን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የተቀናጀ ስርዓት መገንባት፣ ከቴክኖሎጂ ገዢነት ወደ ሀገር ውስጥ አቅም ግንባታ መሸጋገር እንዲሁም ቀጣናዊና አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያና አፍሪካ ከኖርዲክ ሀገራት አዎንታዊ ተሞክሮዎችን እንደሚወስዱ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም የአፍሪካ መፍትሔዎች የአህጉሪቱን እውነታና የትራንስፖርት ፍላጎት ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።
አፍሪካ ወደ ኤሌክትሪክ ሞቢሊቲ የምታደርገው ሽግግር የኢንዱስትሪ ልማት ሞተር እንጂ ለውጭ ምርቶች ሌላ ገበያ መዳረሻ ብቻ መሆን እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡
አፍሪካውያን በጠቅላላው የእሴት ሰንሰለት ውስጥ እንዲሳተፉ የሀገር ውስጥ ገጣጣሚዎችንና አምራቾችን ማጠናከር፣ በምርምርና ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የትራንስፖርት ስርዓቶችን ማስተሳሰር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ለዚህ ትራንስፎርሜሽን የመንግስት ሀብት ብቻውን በቂ አለመሆኑን ጠቁመው፤ በመንግስታት፣ በልማት አጋሮች፣ በንግድ ባንኮችና በግል ባለሀብቶች መካከል ጠንካራ አጋርነት መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ጉባኤው ከውይይት ባለፈ ወደ ተግባራዊ እርምጃዎች የሚወሰዱበት፣ ግልጽ ግቦች የሚቀመጡበት እንዲሁም የልማትና ቴክኖሎጂ አጋሮች ትብብር የሚጠናከርበት መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።