የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ነው
አዳማ፤ መስከረም 5/2019 (ኢዜአ) ፡- የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ የስንዴ ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ለኢዜአ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የስንዴ ልማት እሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ የስንዴ ሰብሉ ድርቅን፣ ከፍተኛ ሙቀትን፣ ተባዮችንና ያልተጠበቀ የዝናብ መዛባትን የሚቋቋሙ የምርጥ ዘር ዝርያዎችን መጠቀም ላይ እንደሚያተኩርም ተገልጿል።
በፕሮጀክቱ በስንዴ ልማቱ ላይ የሚካሄዱት የድጋፍና ክትትል ተግባራቱ በምርት ላይ ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ ሙሉ የልማት የእሴት ሰንሰለቱን የሚያካትት መሆኑም እንዲሁ።
ይህ አሰራር ለገበሬዎች ከዘርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ጀምሮ እስከ ሰብል ስብሰባ፣ ማከማቸት፣ ማቀናበርና ምርቱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እስከ ማቅረብ ያሉትን ሙሉ ሂደቶች ያቃልላል ተብሏል።
በአጠቃላይ ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያመጣው ተጽዕኖ ሳትበገር የስንዴ ምርቷን በማሳደግ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥና ወደ ውጭ የመላክ አቅሟን ለማጠናከር እያደረገች ያለችውን የተቀናጀ እንቅስቃሴ የሚደግፍ ፕሮጀክት መሆኑ ነው የተገለጸው።
በግብርና ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አብዱልሰመድ አብዶ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ነው።
በዚህም በክልሎቹ የሚገኙ 76 ወረዳዎችና 1 ሺህ 129 ቀበሌዎችን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ለአምስት አመታት ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ ፕሮጀክት በአካባቢዎቹ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ስንዴ አምራች አርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች መካከል የዘር ግብዓት አቅርቦት ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም በየደረጃው ከሚገኙ የግብርና ምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በተደረገባቸው ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የዳቦና የመኮሮኒ ስንዴ ዘርን በጥራት በማምረት በፕሮጀክቱ ለታቀፉ አርሶ አደሮች ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
ይህም የመነሻ ዘር አቅርቦት ከማሻሻል ባለፈ የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማስቻሉን አመላክተዋል።
ፕሮጀክቱ ከአፈር ለምነትና ጤንነት ጋር ተያይዞ ስንዴ አምራች በሆኑ አካባቢዎች እያጋጠመ ያለውን ሰፊ የአሲዳማነት ችግርንም ለማቃለል ትኩረት መስጠቱን አስተባባሪው አስታውቀዋል።
በዚህ ረገድ ስለ ኖራ አጠቃቀም ለአርሶ አደሩ በሰርቶ ማሳያ በማሳየት በአሲዳማነት የተጠቃ አፈርን በማከም ምርታማነት እንዲሻሻል በፕሮጀክቱ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የኖራ አቅርቦትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ትላልቅ የኖራ ወፍጮዎች እየተተከሉ ሲሆን፣ ለአፈር ለምነት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ስራም ተያይዞ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ለመስኖ ልማት አመቺ በሆኑ አካባቢዎች የ18 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሜካናይዜሽን ማዕከላትን ከመገንባት ጎን ለጎን በአራቱ ክልሎች 49 ትላልቅና መካከለኛ የስንዴ ማከማቻ መጋዘኖችን የመገንባት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 94 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ይህ ፕሮጀክት፣ መንግሥት የስንዴን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ለያዘው ስትራቴጂ ስኬታማነት ወሳኝ ድርሻ አለው ብለዋል።