ቀጥታ፡

የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እመርታ፤ የአረጋውያን በረከት፣ የታዳጊዎች የተስፋ ማዕድ

ሀገር በታሪክ ሰሪዎችና ባለውለታዎች ጀግኖች አባቶች ገድል፣ በነገ ተስፋዎች ጽናት ትገነባለች፤ በጠንካራ ተቋማትና ተስፋን በሰነቁ ፕሮጀክቶች ትጸናለች።

የመደመር መንግሥት የዜጎችን ማኅበራዊና ምጣኔ-ሀብታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከነደፋቸው ውጥኖች መካከል ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ።

ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ በተማሪዎች ምገባ እና በወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብቻ የተመረኮዙ አይደሉም፤ ይልቁንስ የሀገር ባለውለታዎች ካስማ፣ የነገ ተስፋዎች ማገር ናቸው።

የመደመር መንግሥት ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን ቀዳሚ አጀንዳው ሲያደርግ፣ የትናንት የሀገር ጀግኖች ውለታ በመመለስ እና ለነገ ታዳጊዎች ብርሃን በመፈንጠቅ ነው።

በኢትዮጵያ በከተማና ገጠር፣ በአዛውንቶችና ወጣቶች መካከል አንዳችም ልዩነት ሳይፈጠር የአካባቢያቸውን የመልማት ጸጋ አውጥቶ መጠቀም የሚያስችሉ የዜጎች ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች ተደራሽ ሆነዋል።

በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና የተቸረው ውጤት አስመዝግባለች፤ ሌሎች ክልሎችም ብዙ ተምረውበታል።


 

መንግሥት በመዲናዋ በ2018 ዓ.ም በትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ ግብር 976 ሺህ 702 ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ቁርስና ምሳ መመገብ የሚያስችል ሥርዓት በማንበር ህዝባዊነቱን በተግባር ገልጧል።

ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ኢኒሼቲቩን እንደ ትምህርት በመውሰድ የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር በመጀመር የተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ የማቋረጥ ምጣኔ ቀንሰዋል፤ የተማሪዎችን ትኩረት በመሰብሰብ ለውጤታማ መማር ማስተማር ሂደት መሰረት ጥለዋል።

የደጃዝማች ወንድይራድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ናታኒም በላይ፣ በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር በመጀመሩ ትምህርቱን በሙሉ ትኩረት ሳያቋርጥ የሚማርበት ዕድል ማግኘቱን ገልጿል።

በትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃ ግብር መጀመሩ ለእናቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ገቢ ማግኘትና የአዕምሮ እርካታ እያገኙ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአፄ ነአኩቶ ለአብ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መጋቢ ወይዘሮ መሰረት እንዳለ ናቸው።


 

በአዲስ አበባ 30 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላትን በማቋቋም ራሳቸውን መመገብ ለማይችሉ አቅመ ደካማ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበት ምቹ ምኅዳር ተፈጥሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 30ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሥራ ሲያስጀምሩ፣ የነዋሪዎችን ሕይወት ለመለወጥና ለኑሮ ምቹ አካባቢን መፍጠር ዋና አጀንዳቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የምገባ ማዕከላትን ማስፋፋት አቅመ ደካማ ወገኖችን ከመመገብ ባለፈ ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የምናሳይበትና ለዜጎች የሥራ ዕድል የምንፈጥርበት ነው ብለዋል።

ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በመዲናዋ ማኅበራዊ ፍትሕን በማንገስ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።

ሀገር ላጸኑ የሃገር ባለ ውለታዎች አባቶችና እናቶች በንጹህ፣ ጽዱና ምቹ ቤት የተደላደለ ሕይወት እንዲመሩ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታኅሣሥ 2016 የአዋሬ መንደር የጋራ መኖሪያ ህንፃ አሰርተው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ለውጥ የሚያመጡ፣ የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ የሚያሻሽሉ እና ሀገር የሚያሻግሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አዋሬን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፤ ዕውቀት፣ ሀብትና ጉልበት ተሰናስለው ለሀገርና ሕዝብ ካስማና ማገር የሚሆኑ ተጨባጭ ውጤቶች ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።

"እንሠራለን፣ ኢትዮጵያን እንቀይራለን፣ ኢትዮጵያን እናበለጽጋለን" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ውብ ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ዕድሉ በኢትዮጵያውያን እጅ ላይ እንዳለ አረጋግጠዋል።

የአቅመ ደካሞችን ቤት መጠገን፣ አለፍ ሲልም አዳዲስ ምቹና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን ከተሟላ የመንገድ፣ የውሃ፣ መብራትና መሰል መሠረተ ልማት ጋር ሰርቶ ማስረከብ የመደመር መንግሥት መገለጫ ሆኗል።

በመዲናዋ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ተሰርተው የተላለፉ ቤቶች ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ታምራት ተመስገን የአካል ጉዳተኛ በመሆኑ በርካታ ፈተናዎችን ማስተናገዱን ገልጿል።


 

ይሁን እንጂ አዲስ በተረከበው ቤት እንደ ልብ መንቀሳቀስና ሕይወቱን ማሻሻል የቻለበት ዕድል እንደተፈጠረለት ገልጿል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው የታደሰላቸው እናት ወይዘሮ ታየሁ መኮንን "ቤት ነው ለማለት እንኳን በማያስደፍር" ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በሸራና በላስቲክ ከተጠጋገነ፣ የግድግዳው አፈር ከሚናድ ቤት ውስጥ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ "ቤቴ በመታደሱ 'ቤቱ እላዬ ላይ ይደረመሳል' ከሚል ሰቀቀን ተላቅቄ፣ ያለ ሀሳብ ጎኔን ማሳረፍ ችያለሁ" ብለዋል።

በነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ከጎዳና ሕይወት ወደ ለውጥ አብነት የተሸጋገሩ ወጣት ልጃገረዶች እልፍ ናቸው።

ማዕከሉ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ሴቶች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሕክምና በማድረግ፣ ዘላቂ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና በመስጠት ሕይወታቸውን የሚያሻሽሉበት ተቋም ነው።

ማዕከሉ በ2016 ዓ.ም ሥራ ከጀመረ በኋላ በአምስት ዙሮች ሦስት ሺህ 259 ሴቶችን በማሰልጠን ወጣቶች ተስፋ እንዳላቸውና ለለውጥ ቅርብ እንደሆኑ በተግባር አሳይቷል።

በነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በ2018 ዓ.ም በአምስተኛ ዙር በዶሮ እርባታ ሥልጠና ወስዳ የተመረቀችው ትዕግስት ፀጋዬ፣ ማዕከሉ ከጎዳና ሕይወት ወጥታ ጠንካራ ስብዕና መገንባት የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላት ተናግራለች።


 

በማዕከሉ የቤት አያያዝ ሥልጠና የወሰደችው መሰረት አበራ በበኩሏ፣ ከጎዳና ላይ ከነበረችበት አሰልቺ ሕይወት ተላቃ ጠንካራ የራስ መተማመን በመገንባት ነገን የምታልም ሴት እንዳደረጋት ገልጻለች።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም