ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡና በብዛት ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል

ዲላ፣  መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው  በጀት አመት ቡናን በጥራት እና በብዛት አዘጋጅቶ ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከወዲሁ ትኩረት መሰጠቱን  የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ገለጸ።

ክልላዊ የቡና ምርት አሰባሰብና ተጓዷኝ ተግባራት ላይ  የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል። 


 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የቡና አመራረትና ዝግጅት እየተሻሻለ በመምጣቱ ምርታማነትና ጥራትን ማሳደግ ተችሏል።

ከክልሉ በተያዘው 2019 በጀት አመት ቡናን በጥራት በማዘጋጀት በብዛት ለማእከላዊ ገበያ ለማቅረብ በየደረጃው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት አመቱ ከ48 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማእከላዊ  ገበያ እንደሚቀርብ አመላክተዋል።

ጥራት ላለው ቡና የተሻለ ዋጋ መቆረጡ የዘርፉን ተወዳዳሪነት አሳድጓል ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን የቡና ላኪዎች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኢያሱ ወራሳ ናቸው።


 

ባለፈው ዓመት ቡናን በጥራት ከማዘጋጀት ባለፈ በጊዜ ለገበያ እንዲቀርብ መደረጉ ተጠቃሚነታችን እንዲረጋገጥ አስችሏል ብለዋል፡፡

በተያዘው ምርት ዘመንም ጥራት ያለው ቡና ለገበያ ለማቅረብ ከወዲሁ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

ቡና ላኪ አርሶ አደር አሰለፈች ጋን በበኩላቸው የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመትም ከማሳቸው የሚያገኙትን የቡና ምርት በጥራት በማዘጋጀት በቀጥታ የገበያ ትስስር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ አምራቾች፣ ላኪ አርሶ አደሮች፣ አቅራቢ ነጋዴዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም