በዞኖቹ በሰላም እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ በሰላም እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ወልድያና ደብረ ማርቆስ ፤ መስከረም 4/ 2019(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በሰሜን ወሎና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች በተጠናቀቀው በጀት አመት በሰላም እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ አበረታች ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
በሰሜን ወሎና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች "አርቆ ማየት፤ አልቆ መስራት" በሚል መሪ ሐሳብ የ2018 በጀት አመት የስራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በሰላም እንዲሁም በማህበራዊና ኢኮኖሚ መስኮች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።
በዞኑ የጸጥታ ሃይሉና በህብረተሰቡ የተቀናጀ ጥረት ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
በዚህም በመንግስት የቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል በርካታ የታጠቁ ኃይሎች መግባታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በስራ እድል ፈጠራ በተከናወኑ ተግባራት ከ180 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በበጋ መስኖ ልማት ከ231 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ዘርፉ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል ።
በዲጂታላይዜሽን ትግበራም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው በተያዘው 2019 በጀት አመት በየዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሰሜን ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ወንድሙ በበኩላቸው የአመራሩን የማስፈጸም አቅም በመገንባት በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ለውጥ እንዲመጣ ተደርጓል ብለዋል።
በዞኑ ከጉባላፍቶና ግዳን ወረዳዎች ነዋሪዎች መካከል አቶ ያለው ገደፋውና ወይዘሮ ደብረወርቅ ማዕረግ፤ እንደገለጹት መድረኩ በተጠናቀቀው በጀት አመት የታዩ ክፍተቶችን በማረም በተያዘው የበጀት ዓመት የተሻለ ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜና የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ እንደገለጹት በ2018 በጀት ዓመት ዞኑ በልማትና መልካም አስተዳደር ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ።
በበጀት ዓመቱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በኢንቨስትመንትና ሌሎች ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አስረድተዋል።
ዞኑ በበጀት አመቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ የዚሁ ማሳያ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በተያዘው በጀት አመት በሁሉም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተስፋዬ በላይ በበኩላቸው በፓርቲው አመራር ሰጪነት በተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በዞኖቹ በተካሄደው መድረክ ከዞን፣ ወረዳና የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል ።