በክልሉ ሀገር በቀል የባህል እሴቶችን ጠብቆ የማልማትና ለትውልድ የማስተላለፍ ስራዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሀገር በቀል የባህል እሴቶችን ጠብቆ የማልማትና ለትውልድ የማስተላለፍ ስራዎች ይጠናከራሉ
ደብረ ማርቆስ ፤መስከረም 4/2019 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል ሀገር በቀል የባህል እሴቶችን ጠብቆ የማልማትና ለትውልድ የማስተላለፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን ዓመታዊ የከሴ አጨዳና እንግጫ ነቀላ በዓል ማጠቃለያ ፕሮግራም በደብረማርቆስ ከተማ ተከብሯል።
የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) እንዳሉት ፤ ክልሉ የበርካታ ባህላዊ እሴቶችና የተፈጥሮ ጸጋዎች መገኛ ነው።
እሴቶችን የመጠበቅ፣ የማልማትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፍ ስራዎች በተጠናከረ አግባብ እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በዞኑ ከነሐሴ 15 ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 3 በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው የከሴ አጨዳና የእንግጫ ነቀላ በዓል ከባህል መገለጫዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባህል የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማዳበር እና ማጠናከር ባለፈ በቱሪዝም ዘርፉ ኢኮኖሚውን የማነቃቃት አቅሙ ከፍ ያለ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩ ባህላዊ እሴቶች በመጤ ባህሎች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ስራ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መንገድ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ እንዳሉት፤ በአካባቢው የሚገኙ የመስህብ ሃብቶችን በመጠበቅና በማልማት የቱሪዝም ዘርፉን የማነቃቃት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በተለይም እንደ ከሴ አጨዳና የእንግጫ ነቀላ አይነት በዓላት የእርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መተሳሰብን የሚያሰርጹ በመሆናቸው ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ብርቄ ይዘንጋው እንዳሉት፤ የዞኑ ማህበረሰብ የአኗኗር፣ የአለባበስ፣ የአጊያጊያጥ መገለጫ የሆነው የልጃገረዶች የከሴ አጨዳና የእንግጫ ነቀላ በዓል በባህላዊ እሴትነቱ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።
በዓሉ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው የቱሪስት መስህብ በሚሆን አግባብ በድምቀት እየተከበረ ነው ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት የኔወርቅ አየለ እንዳለችው፤ በዓሉ የቀደመ ባህሎቻቸን እንድንወርስ አስችሎናል ብላለች ።
በዓሉ የማንንታችን መገለጫ እና ታሪካዊ እሴቶቻችንን እንድናውቅ አድርጎናል ያለችው ደግሞ ወጣት አስካለማሪያም ምታቸው ናት።