ቀጥታ፡

በማእከላዊ ጎንደር ዞን የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር ሆነው እየሰሩ ነው

ጎንደር፤ መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፡- በማእከላዊ ጎንደር ዞን የመንግስትን የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር ሆነው እየሰሩ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

በአማራ ክልል የማዕከላዊ ጎንደር ዞን "አርቆ ማየት፣ አልቆ መሥራት" በሚል መሪ ቃል ያለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ፤ በበጀት ዓመቱ በተለይም በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በፀጥታ አካላት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል ብለዋል።

በተሳሳተ መንገድ ጫካ ገብተው የነበሩ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው እንዲመጡ መደረጉን አንስተው በርካቶች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ህብረተሰቡን በመቀላቀል የልማት አርበኛና የሰላም አምባሳደር ሆነው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የቀድሞ ታጣቂዎቹ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በመሰማራት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመለወጥ ብሎም የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በአስተዳደሩ በኩል አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ መሆኑን አንስተው ሌሎችም ጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የጥፋትን መንገድ ትተው የሰላምን አማራጭ በመቀበል ህዝባቸውን እንዲቀላቀሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዞኑ ከሰላምና ፀጥታ ባሻገር በግብርና፣ በኢንዱስትሪ በማህበራዊ አገልግሎት እንዲሁም በመሰረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ አበረታች ውጤቶች መታየታቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ 22 ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቁመው፤ በግንባታ ላይ የሚገኙ 44 ትምህርት ቤቶችን ለማጠናቀቅም በትጋት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል ሰንደቁ፤ ባለፈው በጀት ዓመት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ቀኑ ቢያድጎ በበኩላቸው፤ የሴቶችን፣ ወጣቶችንና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት።

በ2019 በጀት ዓመትም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱን አስረድተዋል።

ለተከታታይ ሁለት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደሮች አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም