በሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሁለንተናዊ ማንሠራራት ማሸጋገር አስችለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሁለንተናዊ ማንሠራራት ማሸጋገር አስችለዋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፡- ባለፉት ዓመታት በሪፎርም ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሁለንተናዊ ማንሠራራት ማሸጋገር ያስቻሉ መሆናቸውን የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት "በማንሠራራት ወደ ልዕልና" በሚል የፓናል ውይይት መድረክ አካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተገኝተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት 2018 ዓ.ም የሀገሪቱ የማንሠራራት አቅም በተጨባጭ የታየበትና ፈተናዎች ወደ ዕድል እና ስኬት የተቀየሩበት ዓመት ነበር።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ለሀገሪቱም ሆነ ለአፍሪካ ትልቅ አብነት መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በየዘርፉ የተመዘገቡ አመርቂ ውጤቶች ኢትዮጵያውያን የጽናት እና የአይበገሬነት ተምሳሌት መሆናቸውን በተግባር ያስመሰከሩበት እንደነበርም አክለዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁም ትውልዱ በታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ድል መሆኑን አብራርተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አዝመራው አንደሞ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ሀሳብ ከማመንጨት እስከ ማደራጀት፣ ማቀናጀትና ለሀገር የሚጠቅሙ ምክረ-ሀሳቦችን ለማመንጨት የሄዱበት ርቀት የተዋጣ ሀገራዊ ምክክር እንዲካሄድ አስችሏል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የማያግባቡ ጉዳዮችን በምክክር የመፍታት ባህልና ልምምድ እንዲጎለብት መሠረት መጣሉን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኃይማኖት ዘለቀ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ስኬታማ የሪፎርም ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመቆጣጠር ይልቅ ሚዲያዎችን የሚደግፍ፣ የሚከታተልና አቅም የሚገነባ ተቋም እንዲሆን ማስቻሉንም ጨምረው አብራርተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በተለይ የመገናኛ ብዙኃንን አቅም በመደገፍ ረገድ ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም አዲስ የልህቀት ማዕከል በማቋቋም ጭምር በተለይ የባለሙያዎችን የዘርፍ ጋዜጠኝነት አቅም ለማዳበር እየሠራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በዚህም የመቆጣጠርና የመደገፍ ሥራን ሚዛን አስጠብቆ በመሄድ ረገድ የተሻለ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ይህም መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ጥቅምን አክብረው እንዲሠሩ በማድረግ ረገድ መሻሻሎች እንዲመዘገቡ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ የሀገሪቱን የማንሠራራት ሥራዎችን ወደ ላቀ ደረጃና ልዕልና ለማሸጋገር ሁለት መሠረታዊ ተግባራት እንደሚከናወኑ አንስተዋል።
የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የገባችውን ቃል የምትፈጽም ሀገር መሆኗን የሚያሳይ አወንታዊ የሀገር ምስል (Brand) መገንባት መሆኑን ጠቁመው፤ ሁለተኛው ደግሞ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰባሰቡበትንና ቀጣይነት ያለው ስኬት መሠረት የሚጥል የጋራ ሀገራዊ ትርክት መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህን በማሳካት ረገድ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃንና የኮሙኒኬሽን ተቋማት ትልቅ ሚና እንዳላቸው አውስተዋል።
ከዚህ አኳያ የመገናኛ ብዙኃን ዲጂታል ሚዲያን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አሠራራቸውን በመቀየር ሕዝብን ለሀገራዊ ራዕይ ማሰባሰብ ላይ በቀጣይነት ሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።