በክልሉ የፍትህ ሥርአቱን የማዘመንና ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፍትህ ሥርአቱን የማዘመንና ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጅግጅጋ፣ መስከረም 4/2019(ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል በተያዘው በጀት አመት የፍትህ ስርአቱን የማዘመንና ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ።
የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበጀት አመቱን የፍርድ ቤቶች ሥራ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በጅግጅጋ ከተማ አካሂዷል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብዲከሪም አህመድ አደን እንደገለጹት፣ በክልሉ በፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጡን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በተያዘው 2019 በጀት አመት አገልግሎቱን ከማዘመን በተጓዳኝ ተደራሽ የማድረግ ስራም ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ ዞኖች ህብረተሰቡ የዳኝነት አገልግሎትን በቅርበትና በቀላሉ የሚያገኙበት ሥርዓት ይጠናከራል ሲሉም አክለዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አብዲ አሊ፣ የክልሉ የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መሀመድ መሀሙድ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።