ቀጥታ፡

18ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ የሁለተኛ ቀናት ቆይታ

‎የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ከመስከረም 2 /2019ዓ.ም ጀምሮ በተካሔደው 18ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው ይታወሳል፤

‎መስከረም 3 ቀን፣ 2019 ዓ.ም የጉባዔው ሁለተኛ ቀን ‘‘ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት’’ በሚል መሪ ቃል የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተሳተፉበት የተካሔደ ሲሆን፣ ጥምረቱ 140 የጋራ አቋሞችን የያዘ (የኒው ዴልሂ መግለጫ) በማውጣትም የመሪዎቹ ጉባኤ ተጠናቋል።

‎የብሪክስ ኒው ዴልሂ የአቋም መግለጫ የዓለም አቀፍ አስተዳደር ማሻሻያ፣ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ሰላም፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትሥሥርን ያካተቱ ዐበይት ጉዳዮች ላይ የአባል ሀገራቱን የጋራ አቋም ያንጸባረቀ ሲሆን ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት ጥምረቱ በጽኑ እንደሚደግፍ በድጋሚ አረጋግጧል፤ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ብቸኛ እጩ በመሆን ተጨማሪ መቀመጫ እንድታገኝ የሚደረገውን ጥረት በጽኑ እንደሚደግፍም አመላክቷል። በተጨማሪም ሀገሪቱ የዓለም አቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ 32 ለማዘጋጀት የጀመረችውን ተነሳሽነትና ዝግጅት እንደሚደግፉ በጋራ መግለጫቸው አረጋግጠዋል። ጥምረቱ 19ኛውን የብሪክስ ጉባኤ በቻይና አስተባባሪነት እንዲዘጋጅም በጋራ አጽድቋል።

‎ከመሪዎቹ ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከአባልና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን ያካሄዱ ሲሆን፤ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያ መስኮች ትብብር፣ በዲጂታላይዜሽን ዙሪያ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች በጥልቀት ተወያይተዋል።

‎‎በድኅረ ጉባኤ ለመሪዎች በተደረገው የእራት ግብዣ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከተለያዩ የብሪክስ አባል እና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር የታደሙ ሲሆን፤ የሁለት ቀናት የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤን አጠናቅቀው ተመልሰዋል።

‎ለበለጠ ወቅታዊ መረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ማኅበራዊ የሚድያ ገጾች ይከታተሉ:-

ድኅረ ገፅ: https://pmo.gov.et/

‎ፌስቡክ: https://web.facebook.com/PMOEthiopia

‎ኤክስ(ትዊተር): https://x.com/PMEthiopia

‎ዩትዩብ: https://youtube.com/@officeoftheprimeminister-e1878...

#PMOEthiopia

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም